AMN- መስከረም 28/2019 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቧቸውን አዳዲስ የካቢኔ አባላት ሹመት በተመለከተ ባደረጉት ገለጻ፣ የአባላቱ መረጣ ከባህላዊ የመስፈርት አሰራር ወጥቶ በተጨባጭ የመፈጸም ብቃት እና በውጤታማነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም አዲሱ የካቢኔ ሹመት፣ የትምህርት ዝግጅት ብቻ ሳይሆን፣ የሥራ አፈጻጸምና የዜጎች ተጠቃሚነት ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ አዲሶቹን የካቢኔ አባላት ለመምረጥ ዋና ዋና መስፈርቶች ታሳቢ ተደርገዋል::
የትምህርት ዝግጅት ብቻውን በቂ አለመሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የተማሩ ነገር ግን ሀሳብን ወደ ተጨባጭ ተግባርና ውጤት የመቀየር፣ የመከታተልና የዲሲፕሊን ብቃት ያላቸው አመራሮች መመረጣቸውን ገልጸዋል።

በተሰማሩበት የሥራ መስክ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉና ግባቸውን ያሳኩ ግለሰቦች ቅድሚያ እንደተሰጣቸውም አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ እስከ 2050 የሚዘልቅ የረጅም ጊዜ የመደመር ስትራቴጂ ያዘጋጀች ሲሆን፣ አዲሶቹ አመራሮች ይህንን ስትራቴጂ በሚገባ የተረዱና ማንኛውም የሀገሪቱ እድገት ቀጥታ እያንዳንዱን ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆን እንዳለበት የሚያምኑ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በሀገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የብሔር፣ የፆታ እና የእምነት ስብጥርን ባካተተ መልኩ አወቃቀሩ እንዲፈጸም መደረጉንም አንስተዋል።
ሹመት የደስታ ሳይሆን የከፍተኛ ኃላፊነትና የሕዝብ አደራ ሸክም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አዲሱ ካቢኔ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን በመታገል ሕዝብን በቅንነትና በመሠዋዕትነት እንዲያገለግል ጥሪ አቅርበዋል።
በታምራት ቢሻው