AMN- ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና አንድነታችን” በሚል መሪ ሃሳብ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግቢ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሕመድ ሺዴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት፣ የመከላከያ ሚኒስትር መሐመድ ኢድርስ ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ፍቀዱ ተሰማ የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት፣ ዲፕሎማቶች፣ የምክር ቤቶቹ አመራሮችና ሠራተኞች እንዲሁም የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፤ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ሉዓላዊነት፣ የሕዝቦች የጋራ ማንነትና የነፃነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
ሰንደቅ ዓላማ የሁሉም ዜጎች የጋራ መጠለያና የእኩልነት ምልክት በመሆኑ፣ እያንዳንዱ ዜጋ ሰንደቅ ዓላማን የማክበርና ክብሩን የማስጠበቅ ሕገ-መንግሥታዊና ዜግነታዊ ኃላፊነቱን በባለቤትነት ስሜት መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በበርካታ የዓለም ሀገራት የነፃነት ምልክት ሆነው መወሰዳቸውን በመግለጽ ሰንደቅ ዓላማችን የነፃነታችን፣ የድላችንና የታሪካችን አርማ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ሀገሪቱ የጀመረችውን የልማት ጉዞ ለማሳካት ሰላምን መጠበቅና ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከፌደራሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በሁሉም ክልሎች፣ በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ካምፖች እንዲሁም በውጭ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።