AMN – ጥቅምት 8/2019 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የነዋሪዎቻችንን ኑሮና አኗኗር ለማሻሻል በትጋት እየሠራን ነው ሲሉ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ዛሬ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተገነባውን የበጎነት መኖሪያ ሕንፃ ለአቅመ ደካሞችና ለሀገር ባለውለታዎች በደስታ አስረክበናል ብለዋል።

ከዚህ በፊት ለመኖር በማይመች ሁኔታ ይኖሩ የነበሩ ወገኖቻችን ዛሬ በተሟላ መሠረተ ልማት የታገዘ ምቹ መኖሪያ ቤት በማግኘታቸው የኑሮ ጫናቸው ቀንሷል፤ ልባቸውም በደስታና በተስፋ ተሞልቷልም ነው ያሉት።

ለእኛ የቤት ልማት ማለት ሕንፃ መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎችን ክብር ማስጠበቅ፣ የኑሮ ጥራትን ማሻሻልና የተሻለ ነገ መገንባት ነው ብለዋል።
ከንቲባዋ አክለውም ፤ የከተማችንን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለመቅረፍና ለነዋሪዎቻችን ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ምቹና ክብር የተሞላበት ኑሮ ለመፍጠር ጥረታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በደሳሳና ለመኖር በማይመች ቤት ውስጥ ስትኖሩ የነበራችሁ ወገኖቻችን፣ ዛሬ ወደ አዲሱ መኖሪያችሁ በመግባታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ያሉ ሲሆን አዲሱ ቤታችሁ የደስታ፣ የሰላም፣ የክብርና የተስፋ መኖሪያ ይሁንላችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“በጋራ እንሠራለን፤ የነዋሪዎቻችንን ኑሮ እናሻሽላለን!” በሚል ጥሪ ስናቀርብላችሁ፣ በጎ ምላሽ በመስጠት ከጎናችን የቆማችሁና ለዚህ በጎ ተግባር አስተዋጽኦ ያደረጋችሁ የሪል እስቴት አልሚዎችን በተጠቃሚዎች ስም ከልብ እናመሰግናለንም ነው ያሉት።
እንዲህ ያለው አጋርነት የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል የተሻለች ከተማ እንድንገነባ ያግዘናል ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጋራ በመሥራት የተሻለ ኑሮና የተሻለች አዲስ አበባ እንገነባለን ብለዋል።