AMN – ጥቅምት 8/2019 ዓ.ም

37ኛው የቶሮንቶ ማራቶን ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አንስቶ ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ በሁለቱም ጾታዎች 11 የኢትዮጵያ አትሌቶች ይሳተፋሉ።
በሴቶች አይንአዲስ ተሾመ፣ ማሪቱ ከተማ፣ ንግስቲ ሀፍቱ፣ ዘውዲቱ አደራው፣ እልፍነሽ ደምሴ እና ቀበኔ ጫላ ይሳተፋሉ።
በዘንድሮው የሴኤል ማራቶን 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ51 ሴኮንድ በመግባት ያሸነፈችው አይንአዲስ ተሾመ ውድድሩን ያሸንፋሉ ተብለው ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል አንዷ ናት። የገባችበት ጊዜም የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷ ነው።

2 ሰዓት ከ16 ደቂቃ ከ07 ሴኮንድ የግል ምርጥ ሰዓቷ የሆነው ማሪቱ ከተማም ሌላኛዋ የምትጠበቅ አትሌት ናት።
ኬንያውያኑ ሩት ቼቢቶክ እና ቢትሪስ ቼሴሬክ የኢትዮጵያ አትሌቶች ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ድንቃለም አየለ፣ ግዛአለው አያና፣ ልመንህ ጌታቸው፣ ይስማው አጥናፉ እና ፍቃዱ ሊቼ በወንዶች የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።
2 ሰዓት ከ6 ደቂቃ ከ43 ሴኮንድ የግል ምርጥ ሰዓት ያለው ድንቃለም አየለ የአሸናፊነት ግምት ካገኙ አትሌቶች መካከል ይገኝበታል።
ግዛአለው ሌላኛው የሚጠበቅ አትሌት ሲሆን 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ35 ሴኮንድ የግል ምርጥ ሰዓቱ ነው።
በወንዶች የወቅቱ የቶሮንቶ ማራቶን አሸናፊ ኬንያዊ አትሌት ሊዮናርድ ላንጋት እና ሌላኛው የሀገሩ አትሌት ኤልቪስ ቼቦይ በውድድሩ ይጠበቃሉ።
በ37ኛው የቶሮንቶ ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች 44 አትሌቶች ይሳተፋሉ።
ከአትሌቶቹ በተጨማሪ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳታፊ ናቸው።
እ.አ.አ በ1990 የተጀመረው የቶሮንቶ ማራቶን በዓለም አትሌቲክስ እውቅና ያለው ( World Athletics Elite Label Road Race) ውድድር ነው።
በተያያዘም 50ኛው አምስተርዳም ማራቶን ዛሬ ከረፋዱ አራት ሰዓት አንስቶ ይካሄዳል።
በሴቶች የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ አይናለም ደስታ ትጠበቃለች።
መሰረት በለጠ፣ ቡዜ ድሪባ፣ መስታወት ፍቅሬ እና የሺ ካላዩ በውድድሩ ላይ ይሳተፋሉ።
በወንዶች ለሚ ብርሃኑ፣ ፀጋዬ ጌታቸው እና ሃይማኖት አለው የሚሳተፉ ይሆናል።
የአምስተርዳም ማራቶን በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።