AMN- ጥቅምት 11/ 2019 ዓ.ም
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በበጎነት መንደር አዲስ ቤት የተረከቡ ነዋሪዎች ከዓመታት እንግልት በኋላ ያገኙትን እፎይታ እና ደስታ ለኤ ኤም ኤን አጋርተዋል።
በአቃቂ ቃሊቲ አዲስ በተገነባው የበጎነት መንደር ቤት ከተረከቡት መካከል እናት አልማዝ አበራ አንዷ ናቸው፡፡ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት የኖሩበት የቀበሌ ቤት በዕድሜ ርዝማኔ እጅግ አርጅታ ዘማለች፡፡
“ቤቷ አረጀች፤ ምስጥ ወጥቶባት እስከ ግድግዳው ድረስ በላው። በምን አቅማችን እንሥራው? የምናገኛት ገቢ ከእጃችን ወደ አፋችን ናት…” ይላሉ እናት አልማዝ ያለፉትን ችግር ሲያስታውሱ። በክረምት ደግሞ የጎርፍ ስጋቱ በእጥፍ ይጨምራል።
ይህ የእናት አልማዝ ብቻ ሳይሆን የጎረቤታቸው የወይዘሮ ሙሉ ታደሰም መከራ ነበር። በጠበቧ ቤት ውስጥ በርካታ ልጆችና የልጅ ልጆች ተሰብስበው ነበር የሚኖሩት፡፡ በዘመመችው ጎጆ የሚበረታው ቅዝቃዜ ለህመም ተጋላጭ ያደረጋቸው ነበር፡፡፣ የሕፃናት የሥነ-ልቦና ጉዳት ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር ይናገራሉ።
የሁለት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ካሳሁን አለሙም በወቅቱ የነበረው ችግር መልከ ብዙ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ በአንድ አካባቢ ላሉ 15 ቤቶች አንድ ሽንት ቤት ብቻ ይጠቀሙ እንደነበር ነው የሚጠቅሱት።ይህም ከጤና እና ከንጽህና አንጻር በተለይም ለሕፃናት እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር ነው የሚያስታውሱት። ለእናት አልማዝ፣ ለወይዘሮ ሙሉ እና ለአቶ ካሳሁን ቤተሰብ ያ ሁሉ ሀሳብ፣ ጭንቀት እና ስቃይ ዛሬ ታሪክ ሆኗል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበጎ ፈቃድ ተግባር በበጎነት መንደር ፕሮጀክት አማካኝነት፣ እነዚህ አባወራዎች እና እመወራዎች ዛሬ የዘመናዊ መኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን በቅተዋል።
አዲሱን ቤታቸውን ሲረከቡ የተሰማቸውን ደስታ ሲገልጹም በፊት በምኖርበት ቤት በማፈር አዲስ ልብስ ለብሼ ለመውጣት እንኳ እፈራ ነበር የሚሉት እናት አልማዝ ዛሬ ግን በደስታ እወጣለሁ ይላሉ፡፡ ለዚህም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያላቸውን ምስጋና በደስታ ታጅበው አቅርበዋል፡፡
አቶ ካሳሁንም የልጆቻቸውን ፈገግታ በማየታቸው የተሰማቸውን እፎይታ “ትልቅ ለውጥ ነው! በተለይ ከመታጠቢያ እና ከንጽህና መጠበቂያ አንጻር ሙሉ በሙሉ ተለውጠናል። አሁን ልጆቼ የራሳቸው መታጠቢያ እና መጸዳጃ ቤት አላቸው። በነሱ ደስታ እኔ እጅግ ደስተኛ ነኝ”ሲሉ ያብራራሉ።
ኢትዮጵያውያን ስንተባበር የማንወጣው ተራራ እና የማንሻገረው ችግር እንደሌለ ይህ አጋጣሚ ማሳያ ነው።
አዲስ አበባ ከተማን ደረጃዋን የጠበቀችና ውብ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የነዋሪዎችን ሕይወት መለወጥ እና ሰብዓዊ ክብርን ማስጠበቅ ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሰራ ለመሆኑ የእነዚህ እናቶችና አባቶች ደስታ ምስክር ነው።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ