AMN – ጥቅምት 11/2019 ዓ.ም
የትግራይ ክልልን ሰላምና ልማት የሚያደናቅፍ አስተሳሰብ ከስሩ መነቀል አለበት ሲሉ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የጸጥታና ሰላም ጉዳዮች ዋና አስፈጻሚ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር በየነ ገለጹ።
የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር አስፈጻሚዎች ጥቅምት 10 ቀን 2019 ዓ.ም ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ጋር የውይይት መድረክ አካሂደዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር በየነ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይት በመፍታት ወደ ግጭት የሚያመሩ መንገዶችን መዝጋት ያስፈልጋል።
ለትግራይ ወጣቶች ልማትን እንጂ ግጭት አናወርሳቸውም ያሉት ብርጋዴር ጄኔራሉ፤ የትግራይ ወጣት ሰላምን በማስጠበቅ ወደ ልማት በመግባት ድህነትን መዋጋት እንዳለበት አሳስበዋል።
የሕዝባዊ ውይይቱ ዋና ዓላማ፤ የትግራይ ወጣት በሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ያሳለፈውን ስቃይና ውድመት አጤኖ፣ በአዲስ መንፈስ በሰላምና ልማት ግንባታ ላይ በቁርጠኝነት እንዲሠራ ለማድረግ መሆኑን አመልክተዋል።
በክልሉ ማናቸውም ፖለቲካዊ ልዩነቶችና ጥያቄዎች በሰከነና ስልጡን ውይይት፣ እንዲሁም የሕዝብን ፍላጎት ባማከለ መንገድ መከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የትግራይ ሕዝብ ከእንግዲህ ጭቆናን የሚሸከም ጫንቃ የለውም ያሉት ብርጋዴር ጄኔራሉ፣ የሕዝብን ጉስቁልና በማባባስ ሰላምና ልማትን የሚያደናቅፍ አስተሳሰብ ከስሩ መነቀል አለበት ብለዋል።

በሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ምክንያት በትግራይ ክልል የተቋረጡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት፣ ሕዝቡ የሰላምና የደኅንነት ዘብ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ ጉዳዮች ዋና አስፈጻሚ ዶክተር ቴዎድሮስ አረጋይ በበኩላቸው፤ የትግራይ ክልል ሕዝብ የተጎናጸፈውን ወርቃማ ዕድል ሰላምና ልማትን በማስቀጠል መጠቀም እንዳለበት ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የመልሶ ግንባታ ተግባራትን ለማከናወን በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ለዚህም በክልሉ ያሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በማቃለል የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ተቀናጅተው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።