ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ጥቅምት 11/2019 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፣ በከተማዋ በመሠረታዊ የዕለት ተዕለት ፍጆታዎችና በቤት ኪራይ ላይ እየታዩ ያሉ ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎችን ለመቆጣጠርና የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል እየተወሰዱ ባሉ የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሔዎች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

በውይይቱ የሥጋ፣ የምግብ ዘይት፣ የዳቦ፣ የታሸገ ውኃና የቤት ኪራይ ዋጋዎች ላይ የሚታዩ ያልተገቡ ጭማሪዎች ተገምግመዋል።

ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታትና ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን ለማረጋገጥም እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኙ የገለጹ ሲሆን፣ በዚህም፡-

1. የምርት አቅርቦትን ማሳደግ

የመሠረታዊ ፍጆታ ምርቶችን አቅርቦት በመጨመር የዋጋ መረጋጋትን ለማምጣትና ሸማቹ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ሁኔታዎችን ይመቻቻሉ።

2. የገበያ ማዕከላትን ማስፋፋትና የደላላ ሰንሰለትን ማሳጠር

አምራቾችንና ሸማቾችን በቀጥታ የሚያገናኙ የገበያ ማዕከላትን በከተማዋ መግቢያ በሮች ላይ በማቋቋም ምርቶች በቀጥታ ለሸማቾች እንዲቀርቡ እየሠራን ነው። ሕብረተሰቡም ከእነዚህ የገበያ ማዕከላት በመገበያየት የተመጣጣኝ ዋጋ አማራጮችን እንዲጠቀም ይበረታታል።

3. የሸማቾች ማኅበራትን ማጠናከር

የሸማቾች ማኅበራት የምርት አቅርቦትና ጥራት እንዲያድግ ተጨማሪ 500 ሚሊዮን ብር የሚያዝ ተዘዋዋሪ ፈንድ (Revolving Fund) ተመድቧል።

4. የእሑድ ገበያዎችን ማስፋፋት

ሸማቾች መሠረታዊ የዕለት ተዕለት ፍጆታዎቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ የእሑድ ገበያዎችን እናስፋፋለን፤ አቅርቦታቸውን ይጠናከራል።

5. ቁጥጥርንና የሕግ ማስከበርን ማጠናከር

የገበያ ሥርዓትን በሚጥሱና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ቁጥጥርና የሕግ ማስከበር ሥራዎች ይጠናከራሉ።

6. የቤት ኪራይን በተመለከተ የአከራይና የተከራይ ግንኙነት በሕግ፣ በውል ስምምነትና በጋራ ኃላፊነት መመራት አለበት። ዜጎች መብታቸውን በሕጋዊ መንገድ እንዲያስከብሩና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በማስረጃ እንዲያቀርቡ እናበረታታለን ብለዋል።

በተመሳሳይም ተደራሽና ተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ማሳደግ ዘላቂ መፍትሔ እየተሰራ መሆኑን ገለፀዋል።

በውይይታችንም የአቅርቦት ችግሮችን ከመሠረቱ በመፍታት፣ ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን በማረጋገጥና ሕገወጥ የዋጋ ጭማሪዎችን በመቆጣጠር የዜጎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ሕብረተሰቡ አስተዳደሩ ባመቻቻቸው የሸማቾች ማኅበራትና የእሑድ ገበያዎች በመገበያየት የኑሮ ወጪውን እንዲቀንስ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

በተጨማሪም ዜጎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ወይም የገበያ ሕግ ጥሰት ሲያጋጥማቸው በቂ ማስረጃ በማቅረብ ለሚመለከተው የከተማ አስተዳደር አካል ሪፖርት እንዲያደርጉ፣ ከተረጋገጠ መረጃ ውጭ ወሬዎችን ከማሰራጨት እንዲቆጠቡና ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን በጋራ እንዲደግፉ አሳስበዋል።

የዜጎችን የኑሮ ጫና ማቃለልና ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን ማረጋገጥ የጋራ ኃላፊነታችን ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review