AMN- ጥቅምት 11/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ የተከተለችው አዲስ የለውጥ እሳቤ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ (ዶ/ር) አረጋዊ በርሔ ገለጹ።
(ዶ/ር) አረጋዊ በርሔ፣ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ወደቦችንና የመርከብ መስመሮችን ለንግድ፣ ለሀገር መከላከያ እና ለባህር ኃይል ግንባታ በመጠቀም ለዘመናት የዘለቀ የባህር ትስስር የነበራት ሀገር መሆኗን አስታውሰዋል።
ምፅዋ እና አሰብ ታሪካዊ የኢትዮጵያ የባህር በሮች እንደነበሩ የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ሀገሪቱ ወደ ባህር የምታደርገውን ቀጥታ የመውጫ መንገድ ማጣቷ በባህር ጉዳዮች ላይ ያላትን ህጋዊ መብትና ታሪካዊ ቁርኝት እንደማያጠፋው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በህጋዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት ያነሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ጥያቄው ሕጋዊም ታሪካዊም መሠረት ያለው መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስገንዘብ ሥራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው ትስስርና መግባባት ሀገሪቱ ያቀደችውን ግብ ለማሳካት አቅም እየሆነ መሆኑን የገለጹት (ዶ/ር) አረጋዊ፤ የባህር በር ጉዳይ የህዝብ የዘመናት ቁጭት በመሆኑ መብቷን የማታስከብርበት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለ ተናግረዋል።
የባህር ኃይል አቅምን መገንባት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ ለሰፊው ቀጣናዊ የባህር ደህንነትም አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
ይህ አቅም ተጠናክሮ ሥራ ላይ ሲውል ለቀይ ባህር ቀጣና ብቻ ሳይሆን ለመላው የአፍሪካ አህጉር ሰላምና መረጋጋት መሠረት ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችልም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያውያን በሀገር በቀል እውቀትና በጋራ ርብርብ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን የመገንባት አቅም እንዳላቸው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆኑ ጉልህ ማሳያ ነው ብለዋል።
ተመሳሳይ ቁርጠኝነትና ትብብር ሀገሪቱ በባህር በር ጉዳይ ያላትን ትልም ለማሳካትና ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት የምታደርገውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር እንደሚያስችልም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።