AMN – ጥቅምት 12/2019 ዓ.ም
አዲስ አበባ ባለፉት አመታት በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ሊከሰቱ የሚችሉ የዋጋ ንረቶችንና የምርት እጥረቶችን በመከላከል፣ በሸማቹ ማኅበረሰብ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎችን አከናውናለች።
በተለይም ጠዋሪ የሌላቸውንና አቅመ ደካማ ዜጎችን ጨምሮ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ታሳቢ በማድረግ፣ በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ የአቅርቦት መስተጓጎሎች እንዲሁም በደላላ ሰንሰለት ምክንያት የሚፈጠሩ የገበያ ችግሮችን ለመቋቋም ተግባራዊ እርምጃዎችን ወስዳለች።
የገበያ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት፣ በከተማዋ መግቢያ በሮች የገበያ ማዕከላትን በማቋቋም የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ከአምራቾች በቀጥታ ወደ ሸማቾች እንዲደርሱ ምቹ ትስስር ፈጥራለች።
የሸማች ማኅበራትን በማደራጀትና አቅማቸውን በማጎልበት፣ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ለመሠረታዊ ሸቀጦች ድጎማ በመስጠት፣ በየሰፈሩ የሰንበት ገበያዎችን በማዘጋጀትና ለአቅመ ደካማ ዜጎች የምገባ ማዕከላትን በማቋቋም የሸማቾችን ጥቅም ለማስጠበቅ ተሠርቷል።
በተጨማሪም የምርት እጥረት ሲያጋጥም ከክምችት ምርቶችን ለገበያ በማቅረብና የገበያ ሁኔታዎችን በመከታተል ተገቢውን ቁጥጥር እያደረገች ትገኛለች።
የዋጋ መረጋጋትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ዋነኛው መፍትሔ ምርታማነትን ማሳደግና የምርት አቅርቦትን ማስፋት ነው። ለዚህም የከተማ ግብርናን ማጠናከር፣ የአምራቾችን አቅም ማሳደግ፣ የምርት ብክነትን መቀነስና የማከማቻና የማጓጓዣ ሥርዓቶችን ማሻሻል ወሳኝ ናቸውና በዚህ ዙርያ መሠረታዊ ስራዎችን መስራት ተችሏል።

አምራቾችንና ሸማቾችን በቀጥታ ማገናኘት፣ አላስፈላጊ የደላላ ሰንሰለትን ማሳጠርና የገበያ መረጃን በወቅቱ ማሰራጨት የምርት ወጪን ለመቀነስና በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶች እንዲቀርቡ ያግዛሉ። በተመሳሳይ የግሉን ዘርፍና የሸማች ማኅበራትን ተሳትፎ ማጠናከር ተወዳዳሪነትን በማሳደግ የገበያ ፍትሐዊነትን ያጠናክራል።
ለዚህም መፍትሄ የሚሆኑ ስራዎች በሁሉም የከተማዐመግብያ በሮች እና ምርት በየመንደሩ ተደራሽ የሚሆንበት ሂደት ተፈጥሯል።
በአጠቃላይ፣ የከተማዋ ቀድመው የተሰሩ የገበያ ማረጋጊያ ሥራዎች በቅድመ ዝግጅት፣ በተቀናጀ አስተዳደርና በምርታማነት ላይ የተመሠረቱ ሲሆኑ፣ ለዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትና ለዜጎች የኑሮ መሻሻል ጠንካራ መሠረት እየፈጠሩ ይገኛሉ።
ማኅበረሰቡም የተደራጁ የገበያ አማራጮችን በመጠቀም፣ የምርት ጥራትንና ዋጋን በማነፃፀር እንዲሁም ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ሲያጋጥም ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በመስጠት የራሱን ጥቅም ማስጠበቅ ይገባዋል።
ሁላችንም በትብብርና በኃላፊነት በመሳተፍ ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን፣ የምርታማነት እድገትንና የተረጋጋ የኑሮ ሁኔታን እናጠናክር በማለት መልዕክት መተላለፉን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።