AMN- ጥቅምት 15/2019 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ፈጣንና ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለሌሎች ትላልቅ ከተሞች ትልቅ ተምሳሌት ሆኖ እያገለገለ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አሕመድ ሺዴ ገለጹ።
አፈ ጉባዔው ይህንን የገለጹት የእንጦጦ-ፒኮክ የወንዝ ዳርቻ ልማት አካል የሆነውና ከቀጨኔ በአምባሳደርና በኢሬቻ እስከ ባምቢስ የተዘረጋው ግዙፍ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ተመርቆ ለሕዝብ ክፍት በሆነበት ወቅት ነው።
አፈ ጉባዔ አሕመድ ሺዴ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት፤ የወንዝ ዳርቻና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቱ የአረንጓዴ ልማትን ያረጋገጠ፣ የከተማዋን ንጽህናና ጽዳት የጠበቀ እንዲሁም የተሻሻሉ መሠረተ ልማቶችን የገነባ መሆኑን አንስተዋል።
ፕሮጀክቱ የሕዝብን የሥራ እንቅስቃሴና ኑሮ ምቹ በማድረግ የከተማዋን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ እንደቀየረና ሕዝብ፣ ባለሀብት እና የመንግሥት ተቋማት በቅንጅት ሲሰሩ የላቀ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።

በመደመር መንግሥት ባለፉት ስምንት ዓመታት ለከተሞች ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን የጠቆሙት አፈ ጉባዔው፤ ከተሞች የዕድገት፣ የኑሮ ጥራትና ለሥራ ምቹ ማዕከላት እንዲሆኑ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማቱ ከሥራ ዕድል ፈጠራና ከማኅበራዊ ጥበቃ ጋር ተጣጥሞ መሄዱ የከተሞችን ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ እያፋጠነ እንደሚገኝም አክለዋል።
በርካታ ሕዝብ የሚኖርባትን አዲስ አበባ ወደ ምቹ የከተማ አካባቢ የመቀየር ሥራ ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱን በመግለጽ፤ በትምህርት፣ በጤና፣ በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር እንዲሁም ለአነስተኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች መኖሪያ ቤት በማቅረብ ረገድ ትልቅ ማኅበራዊ ልማት መከናወኑን ተናግረዋል።
ይህም በነዋሪዎች መካከል የተቀራረበ ገቢ እንዲኖር፣ ፍትሃዊ ልማት እንዲረጋገጥና የኅበረተሰቡ ኑሮ በከፍተኛ ደረጃ እንዲሻሻል ማስቻሉን ገልጸዋል።
በትዝታ መንግስቱ