በሥራ የተለወጠች ፣ በሽልማት የደመቀች የአፍሪካውያን መኩሪያዋ አዲስ አበባ

You are currently viewing በሥራ የተለወጠች ፣ በሽልማት የደመቀች የአፍሪካውያን መኩሪያዋ አዲስ አበባ

AMN- ጥቅምት 22/2019 ዓ.ም

አዲስ አበባ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ያስመዘገበቻቸው ሁለንተናዊ የልማት ስኬቶች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር አልፈው፣ ዛሬ ላይ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍተኛ ዕውቅናዎችንና ሽልማቶችን እያጎናጸፏት ይገኛሉ።

“አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እናደርጋታለን” በሚል ጽኑ መንፈስ የተጀመሩ ሥራዎች፣ ዛሬ ላይ መዲናዋን የዓለም ትኩረት የምትስብ የብልፅግና፣ የዘላቂ ልማት እና የተወዳዳሪነት ምልክት አድርገዋታል።

📌 የላቀ ተወዳዳሪነቷ ማሳያዎች እውቅናዎች የሸንሃይ አዋርድ እና የሴኡል ስማርት ከተማ ሽልማቶች

አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተቀባይነትና ተወዳዳሪነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የሚያሳዩ ድሎች በየጊዜው እየተመዘገቡ ይገኛሉ።

ትናንት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይፋ እንዳደረጉት ፣ አዲስ አበባ በተባበሩት መንግሥታት የሰፈራ ፕሮግራም እና በቻይና የተዘጋጀውን የ2026 የዓለም ከተሞች ቀን “የሸንሃይ አዋርድ” ሽልማት አሸናፊ ሆናለች።

ሽልማቱ በዘላቂ፣ አካታች፣ ሰው ተኮርና አይበገሬ የከተማ ልማት ውጤታማ ሥራዎችን ላከናወኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተመረጡ ጥቂት ከተሞች የሚሰጥ ታላቅ ዕውቅና ነው።

ይህ ድልም ለከተማዋ የመጀመሪያው አይደለም። በ2024 እ.አ.አ በተመድ የሰፈራ ፕሮግራም እና በደቡብ ኮሪያዋ ሴኡል ከተማ የተዘጋጀውን “የሴኡል ስማርት ከተማ ሽልማት” መጎናጸፏ የሚታወስ ሲሆን፣ በናይሮቢ ኬንያ በተካሄደው የአፍሪካ ስማርት ከተሞች ኢንቬስትመንት ሰሚትም የአፍሪካ ምርጥ ስማርት ከተማ ሽልማት ተቀብላለች።

እነዚህ ተከታታይ ድሎች የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በግልጽ ያሳያሉ።

📌 ዓለም ያመነባቸው የዘላቂና አካታች ልማቶቿ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ዓመታት የነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ከማቃለል ጎን ለጎን፣ ሰብአዊነትንና አካታችነትን ማዕከል ያደረጉ ግዙፍ ሥራዎችን አከናውኗል።

ከእነዚህም መካከል በተለይም ለተማሪዎች እና ለአነስተኛ ገቢ ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የተዘረጋው የምገባ ፕሮግራም በዓለም አቀፍ ደረጃ አርአያ በመሆን አዲስ አበባንና መላዋን ኢትዮጵያ ያስጠራ ስኬት ሆኗል።

ጉዳዩ ሀብታም ወይም ድሃ የመሆን ሳይሆን፣ የመንግሥትን የፖሊሲና የተግባር ቆራጥነት የሚፈልግ መሆኑን ተግብራ በማሳየቷ ፣ በኦክቶበር 2022 ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በምገባ ፕሮግራም ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር በመሆን ሽልማት እንዲሰጣት አስችሏል። ይህ ለአፍሪካም ትልቅ ኩራት ነው።

የከተማ መልሶ ማልማትን ከሰው ተኮር አቀራረብ ጋር በማቀናጀት የነዋሪዎችን ፍላጎት ቅድሚያ መስጠቷ፣ የመኖሪያ ቤቶች አቅርቦትን ማሻሻሏ ፣ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶችን አካታችና የተቀናጀ በሆነ መልኩ መገንባቷ የልማት ሥራዎቿን ልዩ ያደርገዋል።

📌 አረንጓዴ፣ ፅዱ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር መዲና

አዲስ አበባ በኢኮሎጂና በአካባቢ ጥበቃ ረገድም ግዙፍ እርምጃዎችን ወስዳለች።

በሴፕቴምበር 2026 ታዋቂው ዘኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ይዞት በወጣው ዘገባ መሠረት፤ የቦታዎች ስጋት የሚያጠናው አልፋ ጂኦ (AlphaGeo) የተሰኘው ጂኦስፓሻል ኩባንያ በዓለም ላይ ካሉ ትልልቅ ከተሞች የ72ቱን የአየር ንብረት የመቋቋም አቅም ደረጃ ሲመድብ፣ አዲስ አበባ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ከአሜሪካዋ ቺካጎ በመቀጠል ሁለተኛ በመሆን ተቀምጣለች።

በተጨማሪም በደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት መሻሻል ለተከናወኑ ሥራዎች በቦነስ አይረስ የC40 ከተሞች የብሉምበርግ ሽልማት የተበረከተላት ሲሆን፣ አፍሪካ ከሚገኙ 10 ፅዱ ከተሞች አንዷ ለመሆንም በቅታለች።

በጁን 2023 የብሉምበርግ ብስክሌት መሰረተ ልማት ኢንሺዬቲቭ ሽልማት ካሸነፉ 10 የዓለማችን ከተሞች አንዷ በመሆን የ400 ሺህ ዶላር ተሸላሚም ሆናለች።

በመንገድ ደኅንነትና ፍጥነት ማስተዳደርም በዓለም አቀፍ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች።

እነዚህ ሁሉ ድሎችና ዓለም አቀፍ ዕውቅናዎች በመንግሥት ቆራጥነትና በከተማ አስተዳደሩ 24/7 ሥራ የመምራት ትጋት ፣ በባለሙያዎች ጥረት እና በመላው የከተማዋ ነዋሪዎች ቀና ትብብር ለተመዘገቡት የላቀ የልማት ከፍታዎች የተሰጡ ናቸው።

በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ፣ በአካባቢ ጥበቃና ንፅህና ከዓለም ሁለተኛ፣ በዘላቂ የከተማ ልማት የሸንሃይ ሽልማት ባለቤት እንዲሁም በስሉጥ (ስማርት) ከተማነት አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነችው አዲስ አበባ ፣ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካ ኩራት ሆና እየገሰገሰች ትገኛለች።

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review