ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሰላምና የጋራ ደህንነት ያላትን ታሪካዊ ሚና በቁርጠኝነት አጽንታ ትቀጥላለች – ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሰላምና የጋራ ደህንነት ያላትን ታሪካዊ ሚና በቁርጠኝነት አጽንታ ትቀጥላለች – ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ

AMN- ኅዳር 1/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሰላምና የጋራ ደህንነት ያላትን ታሪካዊ ሚና አጽንታ እንደምትቀጥል የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል ሃላፊ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ ገለፁ።

የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ የአጋሮች ቀን “በሰላም ላይ ኢንቨስት ማድረግ ለዓለም አቀፍ ደህንነት ጽኑ አጋርነትን መገንባት” በሚል መሪ ሐሳብ ተከብሯል።

በመድረኩ የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል ሃላፊ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮችን እና አጋር ድርጅቶች ተገኝተዋል።

የማዕከሉ ሃላፊ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ1951 የኮሪያ ጦርነት ጀምሮ በኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ላይቤሪያ፣ ቡሩንዲ፣ ዳርፉር፣ አብዬ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ባካሄደቻቸው ተልዕኮዎች ለዓለም አቀፍ ሰላም የብዙ አሥርታት አስተዋጽኦ ማበርከቷን ገልጸዋል።

የሀገሪቱ ለዘመናት የዘለቀው የሰላም ማስከበር ታሪክ የተገነባው በሙያተኝነት፣ በዲሲፕሊን እና መስዋዕትነት ላይ መሆኑን ተናግረው፤ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ገዛኸኝ ፍቃዱ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ እንደ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ሚናው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህም የመከላከያ፣ የፖሊስ እና የሲቪል አባላትን ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ለተለያዩ ተልዕኮዎች እያዘጋጀ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን የካበተ የሰላም ማስከበር ልምድ ወደ እውቀት፣ ምርምር እና ስልጠና በመቀየር ለአፍሪካ እና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚያቀርብ ዋና መድረክ ለመሆን አቅዶ እየሰራ እንዳለ ተናግረዋል።

ዘመናዊ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ጥልቅ ትብብርንና ቴክኖሎጂን የሚጠይቁ በመሆናቸው ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በስልጠና፣ በምርምርና በቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ በበኩላቸው ለአፍሪካ እና ለዓለም ሰላምና መረጋጋት የአጋርነት መንፈስን ማደስ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የተጠናከረ አጋርነት ለቀጣይ ተልዕኮዎች ጠንካራ መሰረት እንደሚጥል በመጠቆም በጋራ በመስራት፣ አዳዲስ እውቀቶችን በመለዋወጥ እና በተለያዩ መንገዶች የእርስ በእርስ ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ማስገምዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review