AMN – ኅዳር 3/2019 ዓ.ም
በካናዳ ቶሮንቶ ዮርክ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ ተወካይ የሆኑት ፕሮፌሰር ዳውን ባዝሊ፤ የኢትዮጵያ የቡና ሀብት እና የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል ጥረት ለዓለም አርአያ መሆኑን ገልጸዋል።
31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP31) «ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬ እና ፍትሃዊ መጻኢ ዘመን» በሚል መሪ ቃል በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።
ፕሮፌሰር ባዝሊ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ በመሆኗ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያበረከተችውን ታላቅ አስተዋጽኦ እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ረገድ እየወሰደች ያለውን አርአያነት ያለው እርምጃ አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ለዓለም ቡናን የሰጠች ሀገር መሆኗን የጠቆሙት ተመራማሪዋ፤ የዓለም የቡና ዝርያዎች መገኛ የኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች መሆናቸውን አንስተዋል።
የቡና ዝርያዎች የሚበቅሉት በተወሰነ የዓለም ምህዳር ውስጥ ብቻ በመሆኑ፣ የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ምርት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያደረሰ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተፈጥሮ ሀብቷን እንዲያገግም በማድረግ በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ረገድ እጅግ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራች መሆኑን በመጥቀስ ለዚህ ስኬት አድናቆታቸውን ችረዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በመተግበር ረገድ እያሳየችው ያለው አሠራር ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትልቅ አርአያ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ባዝሊ፣ ቀጣይነት ያለው የቡና ምርት እንዲኖር በምርምር የተደገፈ ሥራ መሠራት እንዳበት አስገንዝበዋል።
ሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተፈጥሮ መፍትሔዎችን መጠቀሟ ለሌሎች ሀገራት አርአያ ሊሆን እንደሚችል የገለጹ ሲሆን፣ በአረንጓዴ አሻራ የሚሠሩ ሥራዎችም ለአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች ሁነኛ መፍትሔ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በካናዳ ቶሮንቶ ትልቅ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ እንደሚገኝ የጠቀሱት ፕሮፌሰር ባዝሊ፣ ከሠላሳ ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ወደ ካናዳ ከመጡ ተማሪዎች የተቀበሏቸውን ባህላዊ የቡና ዕቃዎች አሁን ድረስ በቤታቸው እንደሚጠቀሙ በኩራት ተናግረዋል።
የሰዎች መገኛ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ መምጣት ሰዎች ከየት እንደመጡና ወዴት እንደሚሄዱ እንደሚያስታውሳቸው በመጥቀስም፣ የሁላችንም የሰው ልጆች መነሻ ቤታችን የሆነችው ኢትዮጵያ ከየት እንደተነሳን እና መዳረሻችን ምን መሆን እንዳለበት በኮፕ-32 ጭምር እንደሚያስታውሰን እንጠብቃለን ሲሉ ገልጸዋል።
በበረከት ጌታቸው