AMN – ኅዳር 13/2019 ዓ.ም
ትናንት በተጨናነቁ ጠባብ መንገዶች፣ በተበከሉ ወንዞችና በደሳሳ ጎጆዎች ትታወቅ የነበረችው የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ፣ ዛሬ የዓለም እንግዶችን አፍ ያስደነቀ የማይታመን ለውጥ በማስመዝገብ የአህጉሪቱ የልማት ተምሳሌት ሆና ብቅ ብላለች።
ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ወደ አዲስ አበባ የመጡ የውጭ ሀገር እንግዶች፣ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉት የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የፈጠሩትን ውበትና ጽዳት ሲመለከቱ በእጅጉ ተደንቀዋል።
ቀደም ሲል ከተማዋን የሚያውቋት ተደጋጋሚ ጎብኚዎች፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የታየውን የመሰረተ ልማት ትስስርና የግንባታ ጥራት “አስገራሚ ትንሳኤ” ሲሉ ገልጸውታል።
ለኤ ኤም ኤን አስተያየታቸውን የሰጡ፣ ከሴራሊዮን የመጣው ባንስ ኮምባሌቢ፣ ከናሚቢያ የመጣችው ሰሰስ ዴላስሎንኮሎ፣ ከቡርኪና ፋሶ የመጣው ሬሞስ ሲንጉሉማ እና ከጀርመን የመጣችው አናሽ ሀይቫ በአዲስ አበባ ለውጥ መደመማቸውን ገልጸዋል፡፡
ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነና በተለያዩ ጊዜያት ደጋግመው መምጣታቸውን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ በመጡ ቁጥር አዳዲስ ለውጦችን እንደሚያዩ ተናግረዋል፡፡
ጎብኚዎቹ፣ የወንዝ ዳርቻዎችን ከመዝናኛና አረንጓዴ ስፍራዎች ጋር፣ የኮሪደር ልማቶችን ደግሞ ከዘመናዊ የትራንስፖርትና የእግረኛ መንገዶች ጋር ተቀናጅተው መስራታቸው እጅግ ማራኪ መሆኑን አንስተዋል።
“ሰርቶ ማሳየት” በሚል መርህ የከተማዋ ነዋሪዎችና አመራሩ በጋራ በመረባረብ ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ጊዜና ጥራት ማጠናቀቃቸው ህዝቡና መንግስት በቅንጅት ተናበው የመስራታቸው ውጤት እንደሆነም ነው የተናገሩት።

የልማት ፕሮጀክቶቹ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል ከመፍጠራቸው ባለፈ፣ የአካባቢውን የንግድና የአገልግሎት ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ ማነቃቃታቸው ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ትልቅ በር ከፋች መሆኑንም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ለውጥ ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን የጠቀሱት ጎብኚዎቹ፣ የሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎችና መሪዎች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ይህንን ስኬታማ ተሞክሮ እንዲቀስሙም ጥሪ አቅርበዋል።
በዘመናዊ መሰረተ ልማቷ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዋነኛ መዳረሻ እየሆነች የመጣችው አዲስ አበባ፣ በጥቂት ዓመታት ብቻ በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በስኬት አስተናግዳለች።
መዲናዋ አሁን ደግሞ ዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ-32) በላቀ ደረጃ ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናክራ ቀጥላለች።
በታምራት ቢሻው