አፍሪካ ለምግብ እና ለንጹህ ውሃ ቅድሚያ ትሰጣለች

You are currently viewing አፍሪካ ለምግብ እና ለንጹህ ውሃ ቅድሚያ ትሰጣለች
  • Post category:አፍሪካ

AMN- የካቲት 6/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ካለው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን፣ “የህጻናትን ህይወት ለማዳን ለአመጋገብ ስርአት ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት” በሚል መሪ ሀሳብ የጎንዮሽ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

መድረኩን ያስተናገዱት የሌሴቶ ንጉስ እና የአፍሪካ ሕብረት የአመጋገብ ዘርፍ አምባሳደር ንጉስ ሌትሲ III ሲሆኑ፣ ከሕብረቱ ኮሚሽንና ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የህጻናትን ህይወት ማዳን አህጉራዊ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ አፍሪካ ለምግብ እና ለንጹህ ውሃ ቅድሚያ እንደምትሰጥ አስገንዝበዋል።

በአፍሪካ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከ18 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በምግብ እጥረት፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት ማነስና በተላላፊ በሽታዎች ምክንያት የመሞት ስጋት ውስጥ እንደሆኑም በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡

መድረኩ የሕብረቱ የ2026 መሪ ቃል ከሆነው “ዘላቂ የውሃ አቅርቦት እና የንጽህና ሥርዓት” ጋር በመቀናጀት፣ አመጋገብን፣ ንጹህ ውሃን እና የጤና አገልግሎትን ያጣመረ አሰራርን እንደሚያበረታታ ተገልጿል።

የመንግሥታት መሪዎች፣ የጤና እና የፋይናንስ ሚኒስትሮች የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ወደ ተግባራዊ የኢንቨስትመንት ዕቅድ ለመቀየርና አዳዲስ የፋይናንስ ምንጮችን ለማሰባሰብ በሚቻልበት ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review