የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲያደርግ አሳሰበ

You are currently viewing የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲያደርግ አሳሰበ

AMN- ታህሣሥ 22/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ህወሓት በኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነምግባር እዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1332/2016 መሠረት በልዩ ሁኔታ መመዝገቡ ይታወቃል።

በአዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀጽ 3 መሠረት በልዩ ሁኔታ የተመዘገበ ፖርቲ ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ ያዛል።

ቦርዱም የፓርቲውን በልዩ ሁኔታ መመዝገብ ባሳወቀበት ነሀሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ቁጥር አ1162/11/15180 በግልፅ እንዳስቀመጠው ፓርቲው ይሀው ደብዳቤና የምዝገባ ሰርትፊኬት ከደረሰው አንስቶ ባሉት ስድስት ወራቶች ውስጥ የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባውን ማድረግ አንዳለበት አስታውቋል።

በሌላም በኩል አዋጅ ቁጥር 1332/2016 ዓ.ም ለማስፈፀም ባወጣው መመሪያ ቁጥር 25/2016 አንቀፅ 12 መሰረት በተጠቀሰው አዋጅ መሰረት በልዩ ሁኔታ የተመዘገበ የፓለቲካ ፖርቲ ምዝገባውን ካገኘበት ጊዜ አንስቶ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ እንዳለበት ያዛል።

ፖርቲው ከፍ ብሎ የተመለከተውን የአዋጁንና የመመሪያውን ድንጋጌዎችና ቦርዱ ልዩ ምዘገባ ሰርትፊኬቱን ሲሰጠው በፃፈው ደብዳቤ ላይ የተገለፀውን በስድስት ወር ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ የሚለውን ግዴታ ያለተጨማሪ ማሳሰቢያ መፈፀም እንዳለበት የሚታመን ቢሆንም ቦርዱ ለፓርቲው ነሀሴ 3 ቀን በቁጥር አ1162/11/15180፣ ነሀሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥር አ1162/11/15209 እና ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም በቁጥር *1162/11/15278 በፃፋቸው ደብዳቤዎች ላይ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማከናወን ጠቅላለ ጉባኤውን እንዲያደርግ አስታውቋል።

ፓርቲው በልዩ ሁኔታ የተመዘገበው ነሀሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም በመሆኑ ጠቅላላ ጉባኤውን እስከ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም እንዲያደርግ ይጠበቃል። በሌላ በኩልም ለዚሁ የጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅት የሚያስፈልገውን የቅድመ ጉባኤ ዝግጅት የተመለከቱ ስራዎችን ቦርዱ መከታተል እንዲችል ፖርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ከማድረጉ 21 ቀናት በፊት ጉባኤው የሚደረግበትን ቀን ለቦርድ እንዲያሳውቅ የሚጠበቅ ነው። ይሁንና ይህ ደብዳቤ አስከተፃፈበት ቀን ድረስ ፓርቲው ከተመዘገበ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ የሚያስችለውን እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ቦርዱ አያውቅም።

በመሆኑም ፓርቲው በልዩ ሁኔታ ከተመዘገበበት ከነሀሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ የሚገባው ወቅት ሊገባደድ ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ የቀረው በመሆኑ ፓርቲው ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በልዩ ሁኔታ በተመዘገበበት አዋጅ፣ አዋጁን ለማስፈፀም የወጣው መመሪያና ቦርዱ ከነሀሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያየ ጊዜ ለፓርቲው በፃፈው ደብዳቤዎች ላይ የተሰጡ ውሳኔዎች በማክበር በቀረው አጭር ጊዜ የጠቅላለ ጉባኤውን እንዲያደርግ ቦርዱ በጥበቅ ያስታውቃል።

ይህ በሕግ ፓርቲው ላይ የተጣለ ግዴታ በወቅቱ ሳይፈፀም ቢቀር ቦርዱ ሕጉን መሠረት በማድረግ ተገቢ ነው የሚለውን ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን ከወዲሁ በአክብሮት ያስገነዝባል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review