የኃይል ስርቆት በፈፀሙ ደንበኞች ላይ እርምጃ ተወሰደ

AMN – ጥር 6/2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደቡብ አዲስ አበባ ሪጅን ቆጣሪዎችን በመነካካት የኃይል ስርቆት በፈፀሙ የወፍጮ ቤት፣ የዳቦ እና የእንጀራ መጋገሪያ ቤት ደንበኞች ላይ እርምጃ መውሰዱን ገለጸ፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 18 ዘመናዊ ቆጣሪዎች ላይ የኃይል ስርቆት የተፈፀመበት ሲሆን፣ በስርቆት ያጣውን ከ4 ሚለየን ብር በላይ የኃይል ፍጆታ ሂሳብ ገንዘብ ማስከፈሉን የሪጅኑ የኢነርጂ ማኔጅመንት ኃላፊ አቶ ለሚ አዱኛ ተናግረዋል፡፡

አቶ ለሚ አክለውም 11 ሥርቆት የፈፀሙ ድርጅቶች ላይ ከ5 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር ቅጣት እንዲቀጡ ማድረጉንና በስርቆት ወቅት ለተበላሹ ቆጣሪዎች 18 ሺህ ብር እንዲከፍሉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የኃይል ስርቆት መረጃው የተገኘው ተቋሙ በሚጠቀመው መተግበሪያ አማካኝነት ሲሆን በዚህ ዓመት ብቻ በኃይል ስርቆት ላይ በተሳተፉ ስምንት ደንበኞች ላይ ክስ ተመስርቶ ክትትል እየተደረገባቸው እንደሆነና ሦስቱ በሂደት ላይ መሆናቸውን ሃላፊው መናገራቸውን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review