AMN- ነሐሴ 9/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተቻቸው ስጦታዎች መካከል ቡና የላቀ ስፍራን ይይዛል።
ቡና ለኢትዮጵያውያን የማኅበራዊ ሕይወታችን አንኳር እና የምጣኔ ሀብታችን የጀርባ አጥንት ነው።

በቅርቡ ከዘርፉ የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ ቡና በኢኮኖሚው መስክ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ሲደርስ፣ ከቤት እፎይታ ጀምሮ እስከ ማኅበራዊ ህብረታችን ድረስ ያለው ፋይዳውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ መጥቷል።
የኢትዮጵያ የቡና ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ውስጥ በማምረትም ሆነ በውጭ ገበያ የገቢ አሰባሰብ ረገድ አዲስ ታሪክ እየፃፈ ይገኛል።

የኢትዮጵያ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ሀገራችን ከቡና ንግድ የምታኘውን ገቢ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችላለች።
የኢትዮጵያ የቡና ማዕበል አዳዲስ ሪኮርዶችን እየሰበረ ሲሆን፣ በቅርቡ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ብቻ ከ 3 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ከቡና ንግድ ተገኝቷል።

ይህም ከቀድሞው አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ዕድገት ያሳየ የሀገሪቱን አጠቃላይ የውጭ ንግድ ገቢ ጉልህ ድርሻ የሚሸፍን ነው።
የምርታማነት ማሻሻያዎች፣ የግብይት ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ የማድረግ ጥረቶች፣ የጥራት ቁጥጥር ማሻሻያዎች እና እንደ ቻይና ያሉ አዳዲስ ግዙፍ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች በታሪፍ ነፃ ገበያ መፈጠራቸው ለዚህ ዕድገት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።
መንግሥት አሁን ላይ ደረጃውን እና ጥራቱን በማሻሻል በቀጣዮቹ ዓመታት ገቢውን ለማሳደግ አዳዲስ ስልቶችን እየተገበረ ይገኛል።

የቡናን ያህል ሰዎችን የሚያቀራርብ፣ ሀሳብን የሚያለዋውጥ እና ማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክር ሌላ ሰብል ወይም መጠጥ ማግኘት አስቸጋሪ ነው።
ቡና በኢትዮጵያዊያን ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የሚጫወተው ሚና ኢኮኖሚያዊ ከመሆኑ እጅግ የላቀ ነው።
ቡና ማለት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የሰላም፣ የፍቅርና የመተሳሰብ መገለጫ ነው።
በቀን ውስጥ ቢያንስ አንዴ ወይም ሁለት ጊዜ በሚዘጋጀው የቡና ማዕድ ዙሪያ የቤተሰብ፣ የጎረቤትና የጓደኛ ግንኙነቶች ይጠናከራሉ።

የችግር ጊዜ መወያያ፣ የደስታ መጋሪያ እና የሰላም ማውረጃ የሚሆነው ይህ ማዕድ ማኅበራዊ ትስስራችንን የጸና አድርጎታል።
ከቤት ውጭ ባሉ የቡና ቤቶችና መደብሮች ውስጥ ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣ ምሁሩና ሠራተኛው በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ ስለ ሀገር ጉዳይ፣ ስለ ስፖርት፣ ስለ ፖለቲካ እና ስለ ማኅበራዊ ሕይወት የሚወያይበት መድረክ ቡና ነው።
በየትኛውም የሀገሪቱ ማዕዘን ይሁን በከተማና በገጠር፣ እንግዳ ሲመጣ በመጀመሪያ የሚቀርበው የክብር መግለጫ ቡና ነው፤ “እባክዎ ቡና ይጠጡ” ማለት የሰላምታና የክብር ሁሉ መጀመሪያ ነው።

የቡና የምርትና የገቢ ዕድገት የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ ጽኑ መሠረት እና የነገ ተስፋ የሚያሳይ ድንቅ ማሳያ ነው።
ከዚህ ጎን ለጎን ቡና በማኅበራዊ መስተጋብራችን ውስጥ ያለው ፋይዳ ሕዝባችንን በአንድነት አስተሳስሮ የሚያቆይ የማይናወጥ ማሕበራዊ ገመድ ነው።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ