በመዲናዋ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ሀገርን ከማስተዋወቅ ባለፈ የኢኮኖሚ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ነው:- የባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ

AMN – ጥር 6/2017 ዓ.ም

በመዲናዋ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት የቱሪዝም ዘርፍን እና ሀገርን ከማስተዋወቅ ባለፈ የኢኮኖሚ ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ መሆኑን የአዲስ አበባ የባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ፣ታሪካዊ ቅርሶችን እንዲሁም የማይዳሰሱ ትውፊቶችን በአግባቡ ለመጠቀምና በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ለዚህ ስኬት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ የቱሪዝም ብራንድና ሎጎ “አፍሪካዊቷ መልኅቅ “በሚል ከሁለት አመት በፊት ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የእንጦጦ ፓርክ፣ አንድነት ፓርክና ወዳጅነት አደባባይን ጨምሮ ማራኪ የቱሪስት መዳረሻዎች እውን ሆነዋል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ሁንዴ ከበደ በመዲናዋ የተገነቡት የቱሪስት መዳረሻዎችና በአዲስ እሳቤ እየተተገበረ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከገጽታ ግንባታ ባለፈ ለኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ እገዛ አድርገዋል ብለዋል፡፡

በተለይም በመዲናዋ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት የቱሪዝም እድገትን ለማሳለጥ እንዲሁም የከተማዋን ገቢ ከማሳደግ አኳያ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡

በመዲናዋ ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ማስፋት መቻሉ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቁጥር በመጨመር ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያድግ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

በቱሪዝም በመዳረሻዎች አስፈላጊው መሰረት ልማት እንዲሟላ መደረጉ ለጎብኚዎች እርካታ ከመፍጠር ባለፈ ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ እያደረገ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡

በተለይም በመዲናዋ የተሰሩ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች፣መሰረተ ልማቶች እንዲሁም የኮሪደር ልማት ስራዎች ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እያስገኙ መሆኑን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል ፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review