AMN – መጋቢት 6/2017 ዓ.ም
የጉምሩክ ኮሚሽን ከየካቲት 27 እስከ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም 339 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውን ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል 281.3 ሚሊየን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 57.7 ሚሊየን ብር የወጭ፣ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን ነው ያመለከተው፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል የተለያዩ ማእድናት፣ አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እፆች፣ መድሃኒት፣ የቁም እንስሳት እና የውጭ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡
በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ እና የወጭ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ሞያሌ፣ አዋሽ እና ድሬድዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ፣ በቅደም ተከተላቸውም 87 ሚሊየን፣ 66 ሚሊየን እና 46 ሚሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ እንደቻሉ አመላክቷል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላት እና ህብረተሰቡ ባደረገው የጋራ ጥረት በፍተሻ እና በበረራ የተያዙ መሆኑንም ገልጿል፡፡
የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 12 ተጠርጣሪ ግለሰቦች እና አምስት ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተጠቁሟል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች እና አመራሮች፣ የክልል እና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ህዝብ ምስጋና ማድረሱን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪውን አቅርቧል፡፡