የኤልኒኖ አየር ንብረት ክስተትን ለመቋቋም አህጉራዊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማጠናከር ይገባል

AMN ሐምሌ 23/2018

የኤልኒኖ አየር ንብረት ክስተትን ለመቋቋም አህጉራዊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

የአፍሪካ ህብረት በፓሲፊክ ውቅያኖስ ሙቀት የሚፈጠር የአየር ንብረት መዛባት (ኤልኒኖ) አስመልክቶ አስቸኳይ ስብሰባውን ዛሬ በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።

በህብረቱ የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ውሃ እና ከባቢ አየር (ADREE) ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ የተዘጋጀው ስብሰባ እ.አ.አ በ2026 ይከሰታል ተብሎ የሚጠበቀውን የኤልኒኖ አየር ንብረት ክስተት ለመቋቋምና አህጉራዊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማጠናከርን ያለመ ነው።

ከፍተኛ የምክክር መድረኩ “የአፍሪካን ቅድመ ዝግጅት፣ የመቋቋም አቅም እና የአየር ንብረት እርምጃዎችን ማጠናከር” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።

የስብሰባው ዋና ትኩረት አፍሪካ ለኤልኒኖ የተቀናጀ ምላሽ እንድትሰጥ የጋራ ትብብርን መፍጠር ነው።

በተጨማሪም በ31ኛው እና በ32ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች (COP31) እና (COP32) ላይ የአፍሪካን ሚና ማሳደግ እና የአህሪቷን አጀንዳዎች ጎልተው እንዲታዩ ማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም ይመክራል።

የአፍሪካ የሜቲዎሮሎጂ ትግበራዎች ልማት ማዕከል (ACMAD) የኤልኒኖ ክስተትን ትንበያ እና በአህጉሪቱ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ በተመለከተ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀርባል።

በተጨማሪም በአየር ንብረት ለውጥ የአፍሪካ ተደራዳሪዎች ቡድን መሪነት አህጉሪቱ በመጪዎቹ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤዎች የምታደርገው ተሳትፎና ለዓለም አቀፉ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ጉባኤ የሚደረጉ ዝግጅቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

የአፍሪካ የውሃ ሚኒስትሮች ምክር ቤትም (AMCOW) ከ 2026 የአፍሪካ ህብረት የዓመቱ መሪ ሀሳብ ጋር የተያያዘ ሪፖርት ያቀርባል።

የአባል ሀገራት ሚኒስትሮችም ስለ ኤልኒኖ ተፅዕኖ እና አህጉራዊ ምላሽ መግለጫዎችን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ስብሰባው በኤልኒኖ ዙሪያ የተዘጋጀውን የድርጊት መርሃ ግብር፣ የባለሙያዎች ሪፖርት እና የጋራ የአቋም መግለጫ እንደሚያፀድቅም ተመላክቷል።

በስብሰባው ከአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት በተጨማሪ የተለያዩ አጋር አካላት ተገኝተዋል።

ኤልኒኖ (El Nino) በፓሲፊክ ውቅያኖስ የውሃ ሙቀት ከመደበኛው በላይ በመጨመሩ ምክንያት የሚከሰት ዓለም አቀፋዊ የከባቢ አየርና የአየር ንብረት መዛባት ክስተት ነው።

የኤልኒኖ ተጽእኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያልተለመደ የከፋ ድርቅን፣ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋንና የሙቀት መጠን መጨመርን በማስከተል በግብርና እና በሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review