የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን “አዲስ ምዕራፍ” የቴሌቪዥን ፕሮግራምን በተመለከተ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን አስመልክቶ መግለጫ አዉጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በኢ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ አዲስ ምዕራፍ በተሰኘ ፕሮግራሙ እሑድ መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም ያሰራጨውን ፕሮግራም ከመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እና ከዘርፉ ሕጎች አንጻር በመገምገም አስተዳደራዊ እርምጃ ወስዷል፡፡
በዚሁ መሰረት በቴሌቪዥን ጣቢያው የቀረበው ፕሮግራም በሐሰተኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ፣ ሕዝብን የሚያሳስትና ጥርጣሬን የሚፈጥር፣ የመገናኛ ብዘኃን አዋጅ 1238/2013፣ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ 1185/2012 እንዲሁም የጋዜጠኝነት ሙያ ስነ-ምግባርን፣ መደበኛ የጋዜጠኝነት አሰራርን የሚጥስ የፓራጆርናሊዝም አሰራርን የተከተለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ጣቢያውም በፕሮግራሙ ዙሪያ ተጠይቆ ለባለሥልጣኑ በሰጠው ምላሽ ያሰራጨው ፕሮግራም ሐሰተኛ መሆኑንና ስህተት መፈጸሙን ገልጿል፡፡
በመሆኑም ባለሥልጣኑ ጉዳዩን መርምሮ በጣቢያው የሚሰራጨው “አዲስ ምዕራፍ” የተሰኘ ፕሮግራም በኤዲቶሪያል አሰራሩ ላይ አስፈላጊውን እርምት ወስዶ ለባለሥልጣኑ እስኪያሳውቅና ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ የአዲስ ምዕራፍ ፕሮግራም በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ መሰረት ከስርጭት ታግዶ እንዲቆይ የተወሰነ እና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው መሆኑን ባለሥልጣኑ ያሳውቃል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን