ጎስቋላ የነበረውን ከተማ እንቀይረው ያልነው ለጋራ ጥቅም፣ ለልጆቻችን ደስታ እና መጻኢውን ዘመን ለማሳመር ብቻ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የትንሳኤ በዓልን በገላን ጉራ ከሚገኙ የካሳንቺስ ልማት ተነሺዎች ጋር አሳልፈዋል፡፡
ይህንን አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፣ ጎስቋላ የነበረውን ከተማ እንቀይረው ያልነው ለጋራ ጥቅም፣ ለልጆቻችን ደስታ እና መጻኢውን ዘመን ለማሳመር ብቻ ነው ብለዋል። የተለወጠችና ከልመና የወጣች ሃገር እውን ከማድረግ ውጪ ሌላ ሃሳብ የለንም ሲሉም ገልጸዋል።
“ይህ አዲሱ ሰፈራችሁ የምትኖሩበት ነው ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ቀድሞ የኖራችሁበት ሰፈራችሁን ሄዳችሁ እንድታዩት እጋብዛለሁ ” በማለት ተናግረዋል።
“ቃል በገባነው መሰረት ካሳንቺስ እጅግ ውብ ሆኗል። ልጆቻችን ተስፋ አላቸው ፣ ከእኛ የተሻለ ህይወት መኖር ይችላሉ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።
“የኢትዮጵያ ትንሳኤ ቅርብ ነው። እኛም እናያለን፣ ልጆቻችንም ይወርሳሉ” ሲሉም አስፍረዋል።