AMN ሚያዝያ 27/2018
በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ለሀገር የላቀ ዐሻራ ላበረከቱ ሙያተኞች ተገቢው ክብር በመሰጠቱ ደስታ ተሰምቶናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ የኪነ-ጥበብ ቤተሰቦች ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ኢትዮጵያን በጥበብ ሙያቸው ላገለገሉ የሀገር ባለውለታዎች የተሠሩ የመታሰቢያ ሐውልቶችን ዛሬ መርቀዋል፡፡
ከምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጥበብ ሀገር ትሠራለች፤ ሀገርም ጠቢብን ታከብራለች ብለዋል።

የሀገር ባለውለታ ለሆኑና በጥበብ ሙያቸው ለሀገራችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለሙያዎች በከተማችን የመታሰቢያ ሐውልቶች ቆሞላቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።
የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች ለሀገር ካበረከቱት አስተዋጽኦ አኳያ የሚዘከሩበት ሐውልት መቆሙን በተመለከተ የኪነ-ጥበብ ቤተሰቦችን አነጋግረናል።

የአንጋፋው አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ባለቤት ወይዘሮ ሮማን በዙ እንደገለጹት፤ ባለቤታቸው በሙዚቃው መስክ ለሀገሩ ለሠራው ሥራ ክብር ለመስጠት ሐውልት በመቆሙ ልዩ ስሜት ተሰምቷቸዋል።
አሁን ለተሠራው ሥራና መንግሥት ላበረከተው አስተዋጽኦ በቤተሰባቸው ስም ምሥጋና አቅርበዋል።

አርቲስት ጥላሁን እና ሌሎች በኪነ-ጥበብ መስክ ዕድገት ላይ የራሳቸውን ሚና የተጫወቱ አንጋፋ ሙያተኞችን ሀገር ስታከብራቸው ማየት ኩራት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ተግባር የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ‘እኔም ለሀገሬ መልካም ከሠራሁ ታሪኬ ይዘክረኛል’ የሚል አስተሳሰብ ኖሮት እንዲሠራ ያበረታታል ብለዋል።
አርቲስት ነዋይ ደበበ በበኩሉ፤ በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች ላይ ለሚገኙ እንቁ ሙያተኞች መንግሥት ለሰጠው ክብር አመሥግኗል።