በርካታ ዜጎችን ለአደጋ የሚያጋልጡ ህገወጥ የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪትና የትምህርት ዕድል እንቅስቃሴዎች እየጨመሩ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በማህበራዊ የመረጃ ትስስር ገፆች በኩል ህገወጥ የውጭ ስራ እና የትምህርት ዕድል ማስታወቂያዎች እየተበራከቱ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመሰል ህገወጥ ተግባር ተታለው በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመታደግና ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ፈታኝ ጥረት እያደረገ ቢሆንም አሁንም በርካታ ዜጎች በህገወጥ እንቅስቃሴው እየተታለሉ ለአደጋ እየተጋለጡ ይገኛሉም ብለዋል።
ከሰሞኑ ሀሰተኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማህተምና ፊርማ በመጠቀም ፈቃድ የተሰጣቸው በማስመሰል የተሳሳተ ማስታወቂያ እያሰራጩ በርካቶችን እያታለሉ ስለመሆኑ ደርሰንበታልም ነው ያሉት አምባሳደር ነብያት።
በነዚህ ህገወጦች ላይ ርምጃ ለመውሰድ ከሚመለከተው አካል ጋር እየተሰራ ይገኛል ያሉት ቃል አቀባዩ ዜጎች እየተበራከተና እየተስፋፋ ካለው ህገወጥ የስራ ስምሪትና የትምህርት ዕድል እንቅስቃሴ ራሳቸውን እንዲጠብቁም አሳስበዋል።
ይህ በ እንዲህ እንዳለም በህገወጥ የስራ ስምሪት ተታለው ወደ ማይናማር በማቅናት አስጊ ህይወት እየተጋፈጡ ከሚገኙ ዜጎች ውስጥ እስካሁን 7 መቶ የሚደርሱትን ወደ ሀገራቸው መመለስ መቻሉን አምባሳደር ነብያት አስታውቀዋል።
በስፍራውም እስከ አንድ ሺ ዜጎች በእስር እና ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ እንደሚገኙ ይገመታል ነው ያሉት።
በአቡ ቻሌ