AMN ግንቦት 7/2018
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የቀድሞው የሮማኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአሁኑ የሀገሪቷ ፕሬዝዳንት ከፍተኛ አማካሪ ዳቺያን ቺዮሎሽን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ኢትዮጵያ ለውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ክፍት ያደረገቻቸው አዳዲስ አሰራሮች ለሮማኒያ ባለሀብቶች ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ከፍተኛ አማካሪው ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከከፍተኛ አማካሪው ጋር የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ውይይት ካደረጉ በኋላ የሮማኒያ ፕሬዝዳንትን መልዕክት ከአማካሪው ተቀብለዋል።
አማካሪ ዳቺያን ቺዮሎሽ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናም ሆነ በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ ለሮማኒያ እጅግ ወሳኝ አጋር ናት።

ዘንድሮ ሮማኒያ በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን የከፈተችበትን 60ኛ ዓመት የምታከብር መሆኑን ያስታወሱት አማካሪው፤ ይህ አጋጣሚ የቆየውን ወዳጅነት ዳግም ለማነቃቃትና የወደፊት ትብብርን ለማጠናከር ትልቅ መሰረት እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ባለፉት አሥርት ዓመታት በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን በሮማኒያ ከፍተኛ ትምህርታቸውን የመከታተል ዕድል ማግኘታቸውን ገልፀው፤ ይህንን ባህል በማስቀጠል አዳዲስ የትምህርት ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም በኢኮኖሚ ትብብር መስክ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ እና የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
በፖለቲካዊ መስኮች እና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ በጋራ መስራት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች እና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ግንኙነቱን ማስፋፋት የጉብኝቱ ዋነኛ ዓላማዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

አማካሪው አዲስ አበባን የጎበኟት ከ12 ዓመታት በፊት እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የታየው ፈጣን ለውጥ እና ዕድገት እንዳስገረማቸው ገልጸዋል።
“ከተማዋ በነዚህ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ያስመዘገበችው ዕድገት እጅግ አስገራሚ ነው፤ ከተማዋን መልሶ ለማወቅ እስኪቸግረኝ ድረስ ተለውጣለች” ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሮማኒያ በኢኮኖሚው ዘርፍም ሆነ በሌሎች የልማት መስኮች የኢትዮጵያ እውነተኛ እና ጠንካራ አጋር ሆና ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላት አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ለውጭ ንግድ እና ለኢንቨስትመንት ክፍት እያደረገች ያለችው አዳዲስ አሰራሮችም ለሮማኒያ ባለሀብቶች ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር መጥቀሳቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።