ኢትዮጵያ እና ጣሊያን ለወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የሚውል የ5 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት ተፈራረሙ

You are currently viewing ኢትዮጵያ እና ጣሊያን ለወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የሚውል የ5 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት ተፈራረሙ

AMN-ግንቦት 6/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የጣሊያን መንግሥት የቀበና ገባር ወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክትን ለመጀመር የሚያስችል የ5 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የቀበና ወንዝ ተፋሰስን ሥነ-ምህዳራዊ እና ማህበራዊ ገጽታ ለማሻሻልና ለማልማት ያለመ ነው።

ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አማካኝነት በ24 ወራት ውስጥ ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

የድጋፍ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የምታደርገውን ሽግግር በቀጥታ ለመደገፍ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት አያያዝን በማጠናከር እና የከተማዋን የአየር ንብረት ለውጥ የመቋቋም አቅም በማሳደግ የ2030 አጀንዳ ግቦችን ለማሳካት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ብክለት ያለባቸውን ሁለት የቀበና ወንዝ ገባሮችን መልሶ ለማልማት ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።

የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን መዘርጋት፣ የዝናብ ውሃ መውረጃዎችን መገንባት ፣ የወንዝ ዳርቻዎችን በጂኦ-ኢንጂነሪንግ ዘዴዎች መከላከል ፣ በአገር በቀል ዕፅዋት እና በማህበረሰብ አገልግሎት መስጫዎች የታጀበ የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ቀጠና መፍጠር ያካተተ መሆኑን መግለጻቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review