ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ወደብ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ፊንላንድ እንደምትደግፍ ገለፀች

You are currently viewing ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ወደብ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ፊንላንድ እንደምትደግፍ ገለፀች

AMN- ግንቦት 7/2018 ዓ.ም

ፊንላንድ ኢትዮጵያ በሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ወደብ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንዲሁም ለቀጣናው ሰላም መረጋገጥ እያደረገችው ያለውን ጥረት እንደምትደግፍ ገልፃለች።

ይህ የተገለፀው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፊንላንድ ፓርላማ አባል የሆኑትን ኪምሞ ኪልጁን እንዲሁም በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ሲኒካ አንቲላን ተቀብሎ በተወያየበት ወቅት ነው።

በውይይቱም በአፍሪካ ቀንድ ስላለው የጂኦፖለቲካ ሁኔታ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት በተለያዩ መስኮች ይበልጥ ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ሁለቱ ሀገራት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ እና ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው፣ ይህንን ግንኙነት በይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምን ለማስፈን እና ቀጣናዊ ልማትና ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ከኢጋድ ጋር በጋራ እያደረገች ያለውን ጥረት አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ስታደርግ የነበረውን ጥረት አጠናክራ አንደምትቀጠል አረጋግጠዋል፡፡

አክለውም ኢትዮጵያ ከታሪክ፣ ከመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ከህዝብ ብዛት እና ኢኮኖሚያዊ እድገት አንጻር እየጎላ የመጣውን የባህር በር ፍላጎቷን በማንሳት የኢትዮጵያን አቋም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምትከተለው ስልት ሰላማዊ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ፣ የአካባቢውን ሀገራት ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚችል መልኩ፣ በዲፕሎማሲያዊ እና በስምምነት መሆኑን ለፊንላንድ የፓርላማ አባል አብራርተዋል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ እንደምትገኝ ጠቁመው፣ መንግስት የወሰዳቸውን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ በኢትዮጵያ ያሉ ኢንቨስትመንት አማራጮችን እና የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ፣ ሀገራዊ ሰላምን ለማፅናት እያደረገች ያለውን ጥረትም ገልፀዋል።

ፊንላንድ በልማት ትብብር፣ በኢንቨስትመንት እና በንግድ ግንኙነት ያላትን ትስስር ለማጠናከር እንደምትሰራ ገልጻለች።

የፊንላንድ ፓርላማ አባል ኪምሞ ኪልጁን ኢትዮጵያ እና ፊንላንድ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው፣ በፊንላንድ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ውስጥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚዋ እና ቁልፍ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በአፍሪካ ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ሰላምና ደህንነት ለማምጣት ለምታደርገው ጥረት ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለመተባበር ያላትን ዝግጁነት እና ቁርጠኝነት ገልጸው፣ በሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ወደብ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ሀገራቸው እንደምትደግፍ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ሲኒካ አንቲላ በበኩላቸው፣ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በዲጅታላይዜሽን ዘርፍ፣ በቴሌ-ኮሙዩኒኬሽን እና በሶላር ኢነርጅ በትብብር እየሰራች መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይ ይህንን አጠንክራ እንደምትቀጥል መናገራቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review