ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

You are currently viewing ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

AMN – ግንቦት 23/2017 ዓ.ም

የቦሌ ክፍለ ከተማ ለሦስተኛ ጊዜ የ“ቦሌ 5150” የጎዳና ላይ ሩጫ አካሂዷል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 “ቃል በተግባር፡ ቦሌ 5150” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የጎዳና ሩጫ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር ) ባደረጉት ንግግር፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄው የሀብት ማሰባሰብ እንቅስቃሴ የቦሌ ክፍለ ከተማ የላቀ ተሳትፎ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አሁን ላይ የግንባታው ሂደት 98.94 ከመቶ መድረሱን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ቀሪውን ግንባታ ለማጠናቀቅ የሚጠይቀውን ከፍተኛ ገንዘብ ለማሰባሰብ የቦሌ ክፍለ ከተማ አመራሮች፣ ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶችና ተቋማት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዓለምጸሐይ ሺፈራው በበኩላቸው፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን የአንድነት ተምሳሌትና የአይቻልም መንፈስና የማሸነፍ መገለጫ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ለሦስተኛ ጊዜ የተካሄደው የ“ቦሌ 5150” የጎዳና ላይ ሩጫ፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ ለግድቡ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያረጋግጥበት መሆኑንን ዋና ስራ አስፈፃሟ ተናግረዋል፡፡

በክፍለ ከተማው ለፕሮጀክቱ መሳካት በሀብት ማሰባሰብ ንቁ ተሳትፎ ላደረጉ አካላትና ለመላው የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ምስጋና አቅርበው አቅርበዋል፡፡

በጎዳና ላይ ሩጫው በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ ለሆኑ ተወዳዳሪዎች እንዲሁም በሀብት ማሰባሰብ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ወረዳዎች የዋንጫ፣ የሜዳሊያ እና የምስክር ወረቀት በክብር እንግዶች ተበርክቶላቸዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review