ወጣት አቤሜሌክ ደጉ በድሬድዋ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ምህንድስና ትምህርቱን እየተከታተለ ባለበት ወቅት በድሬድዋ ከተማ የተመለከተው ብዛት ያለው የፕላስቲክ ቆሻሻ አንድ ሀሳብ እንዲያውጠነጥን መነሻ ሆነው፡፡ የፕላስቲክ ቆሻሻ በሌሎች ሀገራት እንደ ሀብት ይታያል፡፡ በሀገራችንስ እንዴት መልሶ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል? በሚለው ሀሳብ ላይም ከጓደኞቹ ጋር መመካከር ጀመረ፡፡ የአራተኛ ዓመት ተማሪ እያሉም ስራውን ለመጀመር የሚያስፈልገውን የመነሻ ዝርዝር ጥናት አዘጋጅተው እንደጨረሱ ወጣት አቤሜሌክ ይናገራል፡፡
አንድ ዓመት ተኩል የሚሆነውን ጊዜ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የፕላስቲክ ቁሶችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ፋብሪካ ለማቋቋም ጥረት ሲያደርግ የቆየው ወጣቱ፤ በ2012 ዓ.ም ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን “አቤሜሌክ፣ ብርቱካንና ጓደኞቻቸው የፕላስቲክ ማምረት ሽርክና ማህበር”ን መሰረቱ። የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቤሜሌክ እንደሚያስረዳው በወቅቱ አንድ መቶ ሺህ ብር ከኪሳቸው በማውጣት፣ ከአሁኑ ስኬት ባንክ (የቀድሞው የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም) እና ማሽነሪ በሊዝ የሚያቀርበው አዲስ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ አክሲዮን ማህበር የገንዘብና ማሽን እንዲሁም የመስሪያ ቦታ ድጋፍ ተመቻችቶላቸው ነው ስራ የጀመሩት፡፡
ያገለገሉ የፕላስቲክ ቁሶችን ቅርፅ በመስጠት ወደሚፈለገው መጠንና ዓይነት በመለወጥ እንደ ፎቶ ፊልም እየጠቀለለ የሚያወጣ የፊልም ማሽን፣ በሚፈለገው መጠን የሚቆርጥ “ከተር” እንዲሁም የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ በጥቅሉ 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ማሽኖችን በብድር አግኝተዋል፡፡

እነ አቤሜሌክ ለመልሶ መጠቀም የሚውሉ የፕላስቲክ ውጤቶች ወይም ግብአቶችንም ደረቅ ቆሻሻ በመሰብሰብ ከሚሰሩ የፅዳት ሽርክና ማህበራት እና በመልሶ መጠቀም ከተደራጁት ወጣቶች በግዥ ያገኛሉ፡፡ የተሰበሰቡ ቁሶችን በማጠብና በማስተካከል ወደ ፋብሪካው በማስገባት የሚፈለገው ምርት እንዲወጣ ይደረጋል፡፡
በፋብሪካው የችግኝ ማፍያ ፕላስቲኮች፣ ቆሻሻ ማስቀመጫ ወፍራምና ብዛት ያለው ደረቅ ቆሻሻ የሚይዙ ፌስታሎች (ጋርቤጆች)፣ ፕላስቲክ ማሸጊያዎች፣ የፕላስቲክ ቧንቧ (pipe) እና መሰል ምርቶች እንደሚመረት ወጣት አቤሜሌክ ይናገራል፡፡ የምርቶቹ ደንበኛም አብዛኞቹ የመንግስት ተቋማት ሲሆኑ ለሲዳማ፣ ቤኒሻንጌል ጉምዝና ጋምቤላ ክልሎች፣ ለድሬድዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በአዲስ አበባ ደረጃ ለጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል የችግኝ ማፍያ ፕላስቲኮችን አቅርበዋል። የቆሻሻ ማስቀመጫ ፕላስቲኮችን ለሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶችና መሰል ተቋማት ያቀርባሉ፡፡ የፕላስቲክ ቧንቧዎችን ደግሞ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ ተቋማት ያቀርባሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ማህበሩ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ደረጃ ደርሷል፡፡ ካፒታሉ 13 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ በዚህም ከራሳቸው ባሻገር ለ25 ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል። በድርጅቱ የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ሌሊሳ ሶርሳ አንዱ ነው። በማህበሩ በማሽን ኦፕሬተርና መካኒክ በመሆን እየሰራ በሚያገኘው ገንዘብም ቤተሰቡን እየመራ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባለፈ የተለያዩ ማሽኖች አጠቃቀም ክህሎት ማግኘት እንደቻለና ይህም ወደፊት ለሚኖረው ህይወት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው እውቀት ማግኘቱን አስረድቷል፡፡
ደረቅ ቆሻሻን ወደ ሀብት የመለወጡ ስራ ጥራት ያለው ለመልሶ መጠቀም የሚውል ቆሻሻ አቅርቦት ይፈልጋል። በዚህ ረገድ በአዲስ አበባ ከተማ ለመልሶ መጠቀም የሚውል ደረቅ ቆሻሻ በማሰባሰብና በመለየት እየተሳተፉ የሚገኙ በርካታ ማህበራት ይገኛሉ። በአዲስ አበባ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ቱሉ ዲምቱ በተለምዶ አዲስ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ እየሰራ የሚገኘው ሰለሞን፣ ቢያድግልኝና ጓደኞቻቸው የመልሶ መጠቀም ማህበር አንዱ ነው፡፡
የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ወጣት ሰለሞን አጋዠ እንደሚናገረው፣ እሱን ጨምሮ አምስት ወጣቶች በመልሶ መጠቀም የተደራጁት በ2015 ዓ.ም ነበር፡፡ ለስራ መነሻ የሚሆን 40 ሺህ መነሻ ካፒታል በመያዝ ነበር ስራ የጀመሩት፡፡ የውሃ መያዣ ፕላስቲክ (ሀይላንድ)፣ ካርቶን፣ ማዳበሪያ፣ ብረታ ብረትና መሰል ደረቅ ቆሻሻን እንደ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት ካሉ ተቋማት እንዲሁም በየቀኑ ቆሻሻ ከሚሰበስቡ ግለሰቦች በተሰጣቸው ማጠራቀሚያ ቦታ ላይ እየለዩ መልሶ መጠቀም ለሚሰሩ ፋብሪካዎች ያስረክባሉ፡፡
በዚህም ትርፋማ በመሆን ህይወታቸውን በአግባቡ መምራት፣ በኑሯቸው ላይ ለውጥ ማሳየት መቻላቸውን የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ወጣት ሰለሞን ያነሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለሦስት ሰዎች በቋሚነት የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ በየቦታው ለመልሶ መጠቀም የሚሆን ቆሻሻ የሚለቅሙ ከ30 እስከ 40 የሚሆኑ ሰዎችም ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ዓለም አቀፍ እውቅና ያተረፈው ስራ
በአዲስ አበባ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ የመልሶ መጠቀምና ዑደት ማድረግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ባዩሽ ታደሰ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፣ በአዲስ አበባ ከተማ በየቀኑ ከ2 ሺህ 500 ቶን በላይ ቆሻሻ ይመረታል፡፡ የሚመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ በአግባቡ እየሰበሰቡ ከማስወገድ ባሻገር እንደ ሀብት ቆጥሮ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
በ2012 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ መልሶ መጠቀም ራሱን ችሎ እንዲሰራ መመሪያ በማዘጋጀት፣ ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ ባለሙያ ተመድቦና ወጣቶች ተደራጅተው የሚሰሩበት ሁኔታ ተዘረጋ። በ2013 ዓ.ም በመልሶ መጠቀም ላይ የሚሰሩ ማህበራትን በማደራጀት ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ ኮምፖስት በማዘጋጀት፣ ወረቀትና ካርቶን እንዲሁም ፕላስቲክ፣ ብረታ ብረትና ጠርሙስ ደረቅ ቆሻሻ የሚሰበስቡ ማህበራት በየዘርፉ ተደራጅተው ቆሻሻን በመለየት፣ መልሶ መጠቀም ከሚሰሩ ኩባንያዎች ጋር የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ወ/ሮ ባዩሽ እንደነገሩን፣ በአዲስ አበባ በኮምፖስት ማምረት፣ ወረቀትና ካርቶን፣ ፕላስቲክና ብረታ ብረት ነክ ደረቅ ቆሻሻዎችን በመሰብሰብና መለየት 343 ማህበራት ተሰማርተው ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ውስን ቢሆኑም በራሳቸው ደረቅ ቆሻሻን ፈጭተው ለተለያየ አገልግሎት የሚያውሉ አሉ፡፡ አብዛኞቹ ግን ለፋብሪካዎች የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ የፅዳት ሽርክና ማህበራትም ከየቤትና ተቋማት ከሚሰበስቡት ቆሻሻ የሚወገደውንና ለመልሶ መጠቀም የሚውለውን በመለየት ለፋብሪካዎች ያስረክባሉ፡፡

ደረቅ ቆሻሻን መልሶ መጠቀም ስራው ትኩረት አንድም የአካባቢ ፅዳት እንዲጠብቅ፤ በሌላ በኩል ወጣቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ኤጀንሲው ማህበራት የሚሰበስቡት ለመልሶ መጠቀም የሚውል ቆሻሻ ወደ ሀብት የሚለውጡ ፋብሪካዎች ስለሚያስፈልጉ፣ አዳዲስ ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲገቡ የገበያ ትስስር በመፍጠር ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ከሦስትና አራት ዓመት በፊት የውሃ መያዥያ ፕላስቲኮች (ሀይላንድ) ከተሰበሰበና ከታጠበ በኋላ ተፈጭቶ ወደ ውጭ ነበር የሚላከው። አሁን ላይ ግን በመልሶ መጠቀም የሚሰሩ ፋብሪካዎች ተቋቁመው ሀገር ውስጥ የተለያዩ ምርቶችን እያመረቱ ይገኛሉ። ለምሳሌ የፕላስቲክ ውጤቶችን በመፍጨት ገመድ፣ ኮምፎርት ልብስ፣ መጥረጊያ፣ የለስላሳ መያዣዎች፣ ወንበርና ጠረጴዛ ይመረታል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 75 ሺህ 221 ቶን ደረቅ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ተችሏል፡፡ ይህም በዕቅድ ከተያዘው የ72 ሺህ ቶን አኳያ ከፍ ያለ ነው፡፡ በገቢ ረገድም ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል። ይህም በእቅድ ከተያዘው የ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው እንደሆነ ወ/ሮ ባዩሽ ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ደረቅ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም የሚገኘው ገቢ ከዓመት ወደ ዓመት ጭማሪ እያሳየ መጥቷል። በ2013 ዓ.ም ከደረቅ ቆሻሻ መልሶ መጠቀምና ዑደት 141 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ነበር የተገኘው፡፡ በ2014 ዓ.ም ወደ 243 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፣ በ2015 ዓ.ም 985 ነጥብ 1 ሚሊዮን፣ በ2016 ዓ.ም 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡
ወ/ሮ ባዩሽ እንደሚገለፁት ከተማዋ ከምታመነጨው ደረቅ ቆሻሻ ውስጥ 12 በመቶ የሚሆነውን ለመልሶ መጠቀም እየዋለ ይገኛል፡፡ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ ለመልሶ መጠቀም የሚውለው 11 በመቶ የሚሆነው ነበር። ከዚህ ቀደም ደረቅ ቆሻሻን ወደ ሀብት መቀየር የሚቻልበት ስርዓት አልነበረም። አብዛኛው በከተማዋ የሚመነጨው የደረቅ ቆሻሻ ዓይነት ወደ ስርዓት ገብቷል። አሁን ስርዓቱ ስለተዘረጋ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ መስራት ከተቻለ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያ ከጃፓን መንግስት ጋር የተሞክሮ ልውውጥና በጋራ ጥናቶች በመደረጋቸው ወደ ስራ እንዲገባ እንደሚደረግ ወ/ሮ ባዩሽ ጠቁመዋል፡፡
በጃፓን ከሚመነጨው ደረቅ ቆሻሻ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው በመልሶ መጠቀም ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ደረጃ የደረሰችው በአንድ ጊዜ አይደለም፤ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና በረጅም ጊዜ ጥረት እንደሆነ የሚያነሱት ወ/ሮ ባዩሽ፣ አዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም በአጭር ጊዜ ያመጣችው ለውጥ ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ያስደነቀና እንደ ኬንያ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮውን ለመውሰድ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ከተማዋ መምጣታቸውን ወ/ሮ ባዩሽ ተናግረዋል፡፡ አዲስ አበባ በ2015 ዓ.ም በአርጀንቲና ዋና ከተማ ቦነስ አይረስ በተካሄደው በC40 የከንቲባዎች ፎረም የአየር ንብረትን የሚከላከል ተስማሚና መልሶ የመጠቀም አሰራርን የተገበረ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት በመዘርጋት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ መሆኗ ይታወቃል፡፡
በከተማዋ ከሚመነጨው ደረቅ ቆሻሻ ውስጥ የብረታ ብረት፣ ወረቀት፣ ካርቶንና ፕላስቲክ ውጤቶች 18 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ 12 በመቶ የሚሆነው ተሰብስቦ ለመልሶ መጠቀም እየዋለ ይገኛል፡፡ መበስበስ የሚችልና ወደ ኮምፖስት መቀየር የሚችለው ከሚመነጨው ደረቅ ቆሻሻ የስልሳ በመቶ ድርሻ ይይዛል፡፡ በዚህ ረገድ የሚበሰብሰውን ቆሻሻ ወደ ኮምፖስት በመቀየር ረገድ ብዙ ስራ እንደሚጠበቅ ወ/ሮ ባዩሽ ጠቁመዋል፡፡
በከተማዋ ደረቅ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ከህብረተሰቡ ትልቁ የሚጠበቀው ቆሻሻን ከምንጩ መለየት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ግንዛቤዎች ቢፈጠሩም በአግባቡ የሚበሰብስ፣ የማይበሰብስና ጎጂ ብሎ መለየት ላይ ክፍተቶች ይታያሉ። በዚህ ረገድ ልክ መልሶ መጠቀም ላይ ለውጥ ለማምጣት ሁሉም መረባረብ እንዳለበት ወ/ሮ ባዩሽ አስገንዝበዋል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ