መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰዱ ሀገሪቷ ወደ ፊት እንድትጓዝ ማስቻሉን አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ገለጹ

You are currently viewing መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰዱ ሀገሪቷ ወደ ፊት እንድትጓዝ ማስቻሉን አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ገለጹ

AMN- ግንቦት 29/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ መንግስት ደፋር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰዱ ሀገሪቷን ወደፊት እንድትጓዝ ማስቻሉን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ያለው ንግድ እና ኢንቨስትመንት እያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ መንግስት በድፍረት የወሰዳቸው እርምጃዎች ሀገሪቷ ላይ ጠቃሚና ትርጉም ያላቸው ለውጦች አምጥተዋል።

ከማሻሻያዎቹ መካከል የውጭ ምንዛሪ ተመን አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ማሻሻያ በመደረጉ ለበርካታ ዓመታት ያልታየ የውጭ ምንዛሪ ገበያ መረጋጋት መከሰቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ቁልፍ ውሳኔዎችን በማሳለፉ የተገኙ ለውጦች መኖራቸውን ያመለከቱት አምባሳደሩ፣ በዚህም የመንግስትን ጥረት አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ያለው ንግድ እና ኢንቨስትመንት እያደገ መምጣቱን በመግለጽም፣ በቀጣይም በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማስፋፋት ፍላጎት መኖሩን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሰፊ የወጪ ንግድ አቅም እንዳላት ያብራሩት አምባሳደሩ፣ በተለይም የቡና፣ ሻይ፣ ጤፍ፣ አበባ እና የማዕድን ሀብቶችን ወደ አሜሪካ በመላክ የውጭ ምንዛሬ የማግኘት አቅም እንዳላት ጠቁመዋል፡፡

ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የሚገድብ የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ውስጥ ስትንቀሳቀስ መቆየቷን አንስተው፣ አሁን ያለው መንግስት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የወሰደው የፖሊሲ እርምጃንም አድንቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ቡናን ጨምሮ ወደ አሜሪካ የሚላኩ ምርቶችን ለማስፋት ትልቅ ዕድል መኖሩን የጠቆሙ ሲሆን፣ እነዚህን ዕድሎች ለማስፋትም ከኢትዮጵያ መንግስት እና የንግድ ማህበረሰብ ጋር በጋራ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለው ዘላቂ ትብብር የሚደነቅ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ አጋርነት የሚያጎላ መሆኑንም አመላክተዋል።

በተጨማሪም አሜሪካ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ የሚገነባውን አውሮፕላን ማረፊያ በማልማት ረገድ ዕድሎች ለማየት በንቃት የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት ማመላከታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review