የሰው ልጅ በዘመኑ ያሳለፋቸው ክስተቶች፣ ባህሎች፣ ቴክኖሎጂዎችና አጠቃላይ ኑረቶች በርካታ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ትዝታ ሆነዋል፡፡ የተቀሩት ደግሞ መልክና አይነታቸውን ለውጠው፣ ዘምነው ዛሬም ድረስ ለሰው ልጅ ህይወት አስፈላጊ ሆነው፣ ጥብቅ ቁርኝት ፈጥረው ቀጥለዋል፡፡ ግን ሰዎች ትናንትን እና ዛሬን እያነጻጸሩ ያን ጊዜ ትዝ ይልሃል/ትዝ ይልሻል እየተባለ የመወያያና ጨዋታ ርዕስ ይሆናሉ፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ስልክ ነው፡፡
በስልክ አነጋግረኝ በቀጭኑ ሽቦ
ትዝታ እንዲመጣ ደርቦ ደራርቦ… የተባለለት ስልክ በርካታ ትዝታ ያለው፣ የጨዋታ ማድመቂያ፣ በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች የተገለጸ የሙዚቃም ርዕስ ነው፡፡
ወይዘሮ መዓዛ ምትኩ እድሜያቸው ወደ 70 ተጠግቷል፡፡ እርሳቸው ስልክ በእኛ ጊዜኮ ብርቅ ነበር፡፡ በሰፈር ውስጥ ሃብታም የሆነ ሰው ብቻ ነው የሚኖረው። ሩቅ ያለ ዘመድ ስልክ ቁጥር ከጠየቀንም የምንሰጠው የጎረቤታችንን ነበር፡፡ ከዛ ስልክ ተደወለ ተብሎ እንጠራለን፡፡ ከሰው ቤት ሄደን ነበር ዘመዶቻችንን ስልክ የምናናግረው ይላሉ፡፡
ሰው ቤት ሄደን ሚስጥር ለማውራት ችግር ነበር፡፡ በኋላም እኛ ከገዛን በኋላ ልጆች እንዳይደውሉ እንቆልፈው ነበር፡፡ ስልክ የሚወራው ቤተሰብ ወይም ጎረቤት ባለበት ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው ሰው ስልኩን የሚያስቀምጠው ሳሎን ቤት ከቴሌቪዥን ጎን ነበር፡፡ ጥቂት ሰው መኝታ ቤቱ ውስጥ ሊያስቀመጥ ይችላል።
ስለዚህ ከፍቅረኛ ጋር ለማውራት አይመችም፡፡ እንደ አማራጭ በሳንቲም የሚሰራው የግድግዳ ስልክ ነበር፡፡ እርሱም ቢሆን ሰው ከኋላህ ተሰልፎ ተራ ስለሚጠብቅ ምንም አይመችም ነበር፡፡ ምናልባት ለመገናኘት፣ አጭር መልዕክት ለማስተላለፍ እና በኮድ (በሚስጥር) ለመቀጣጠር ካልሆነ በስተቀር የጎረቤቱ ወሬም፣ ቁጥጥሩም፣ ሃሜቱም ከባድ ነበር ይላሉ፡፡
እዚህ ጋር አንድ እውነተኛ ታሪክ እንጥቀስ፡፡ ታዋቂው ድምጻዊ ጎሳዬ ተስፋዬ ባለቤቱን ገነትን ያገኘው በተሳሳተ የስልክ ጥሪ ነው፡፡ ራሷ ሌላ ሰው ጋር ለመደወል ብላ ተሳሳተች፡፤ ከዚያም ወሬው ቀጥሎ ባለትዳር ሆነዋል። ወልደዋል፡፡ ይህን እውነተኛ ታሪክ ራሱ ጎሳዬ ™በተሳሳተ ስልክ” በሚል ርዕስ ሙዚቃ ሰርቶበታል፡፡
በተሳሳተ ስልክ በድንገት ድምጿን
ሰምቼ
ሳወራ ብቆይ ከሷ ጋር ጉዳዬን ትቼ
እጇን የመራው ወደ ስልኬ
ሊያገናኘን ነው ለካ እሱ አምላኬ
አሁን ብናገረው እስኪ እንደው እኔን
ማን ያምነኛል
ሳስበው ደግሞ ለራሴም ግርም ይለኛል… በማለት ታሪኩን በሙዚቃ ጥበብ ከሽኖታል፡፡
በተጨማሪም የድምጻዊ ታደለ በቀለ እና ወይንሸት ሙሉነህ “በስልክ አነጋግሪኝ” የተሰኘው ዘፈን ስለ ስልክ እና የቀደመው ዘመን ብዙ የሚነግረንና የሚያስታውሰን ነገር አለ፡፡
በስልክ አነጋግረኝ በቀጭኑ ሽቦ
ትዝታ እንዲመጣ ደርቦ ደራርቦ…እያሉ ይቀባበሉታል፡፡ እርሷም የከፋትን፣ ያልተመቻትንና በሰው ምላስ ለሃሜት መውደቋን በስልክ ለሩቅ ወዳጇ ትነግረዋለች፡፡
እኛን የታከተን የሰው ነገር ብቻ
አካፍለን በበላን ትርፉ ሃሜት ብቻ…
እያለች፡፡
እርሱም ይመልሳል፡፡ ስሟ በመጥፋቱ በደረሰባት ተገቢ ያልሆነ ሃሜት የእሱም ስሜት መነካቱን እንዲህ ሲል ይነግራታል፡፡
ሸንኮሪየ እኔ ስሜ ይጥፋ እኔ ልታማልሽ
ባጎረስሽው እጅሽ ምነው መነከስሽ
ሸንኮርዬ በዛ በካውያ ጸጉርሽ አይተኮስ
ሸንኮርዬ የሰው አፍ እሳት ነው ኋላም ያው መጠበስ… እያለ ይመልስላታል፡፡ በስልክ በቀጭኑ ሽቦ፡፡
ዛሬ አብዛኛው ሰው ባለስልክ እንዲሆን ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የተንቀሳቃሽ ስልክ (ሞባይል) እና ሲም ካርድ መፈጠር ነው፡፡ በሀገራችን ከገመድ ስልክ ወደ ሞባይል ሽግግር ሲደረግ አንድ አስገራሚ ነገሮች ነበሩት ይላል የደራው መጽሔት፡፡ ለዚህም ሲም ካርድ ሲመጣ ይጠየቁ የነበሩ ከፍ ያሉ መስፈርቶች፣ ሰዎች ሞባይላቸውን ከቀበቶ ጋር በሚታሰር መያዣ ይዘው መንቀሳቀሳቸው፣ በኔትዎርክ ምክንያት ከአዲስ አበባ ውጭ መደዋወል አስቸጋሪ መሆኑ፣ ሲም ካርድ ከሰው መከራየትና የመሳሰሉት ነበሩ፡፡
ወይዘሮ መዓዛ “አሁንማ ትንንሽ ልጆች ሁሉ የራሳቸው ስልክ አላቸው” በማለት ስለትናንት ያላቸውን ትውስታ እና ስለዛሬ ያላቸውን እይታ አጫውተውናል። በፊት በፊት ይላሉ ወይዘሮ መዓዛ የቤት ስልክም ሆነ ሞባይል ብርቅ ነገር ነበር። ምክንያቱም የፍቅር፣ የመልዕክትና የሌሎች መለዋወጫ መንገዱ ደብዳቤ ነበር፡፡ የራሳቸው ፖስታ ሳጥን ቁጥር ያላቸው ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከዚያ የገመድ ስልክ ሲመጣ የፖስታ አስፈላጊነት እየቀነሰ መጣ፡፡ ደብዳቤም ቀርቶ መደዋወል ሆነ።
ከዚያም ሰዎች በስልክ ወደ ሬዲዮ ጣብያዎች ደውለው ዘፈን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለፍቅረኞቻቸውና ለሚወዱት ሰው መጋበዝ ጀመሩ፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮ የስልክ የዘፈን ምርጫ ፕሮግራምን ብዙዎች የሚያስታውሱት ነው፡፡
ዳግም ተክላይ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ቤተሰብ ሞባይል ስልክ የገዙለት የ8ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ነው፡፡ በእርግጥ መጀመሪያ የተገዛለት ስልክ አሁን እንደያዘው ስልክ ዘመናዊ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ዘመናዊ (ስማርት) ስልክ ነው የሚጠቀመው፡፡ በስልኩ እንደ ቲክቶክ፣ ፌስቡክ፣ ዩቱብ፣ ኢንስታግራም፣ ቴሌግራም እና ሌሎችንም የማህበራዊ ሚዲያዎች ይጠቀማል፡፡ ሙዚቃም ከፈለገ የሚፈልገውን ዘፋኝ ስም አስገብቶ ማዳመጥ ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡ ለጓደኞቹ ያዝናናውን ነገር መላክ ከፈለገ ፎቶ መላክ ወይም ሊንክ ማጋራት ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡
ስልክ በድሮ ጊዜ እንዲህ ነበር የሚለውን ከወላጆቹና በአባቱ ጓደኞች መካከል ጨዋታ ሲነሳ አልፎ አልፎ ይሰማል፡፡ በጣም የሚያስቅና የሚያዝናና “እንዲህም ተኑሯል” የሚያስብል ነገርም አለው የሚለው ዳግም “ካስገረሙኝ መካከል መጀመሪያ ጊዜ ሲም ካርድ ለማውጣት የቤት ካርታ ያስፈልግ ነበር የሚለው ነው” ይላል፡፡
ስልክ አሁን በዓመታት ሳይሆን በሰዓታት እየተቀያየረ ነው፡፡ በተለይ ከዘመናዊ የእጅ ስልኮች እኩል የሚፈለፈሉ መተግበሪያዎች፣ የካሜራ ጥራት፣ ምስልና ቪዲዮ የመያዝ አቅም፣ ለአያያዝ ምቹና ቀልጣፋ መሆን በውድድር ታግዘው ትናንትን ወደ ትዝታ ቀይረውታል፡፡
አሁን አብዛኛው ሰው ባለሞባይል ነው። ፍቅርን ለመግለጽ መልዕክት (ቴክስት)፣ በቀጥታ መደወል፣ ከበዙት የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች በአንዱ ድምጽ፣ ምስል ወይም ጽሑፍ መላክ ይቻላል፡፡ ባለስልኮች መልዕክቱን ካልፈለጉ ብዙ አማራጮች አሏቸው። ስልካቸውን መዝጋት ወይም የደዋዩን ቁጥር ብላክ ሊስት መክተት ወይም በማህበራዊ ሚዲያው ደግሞ ብሎክ ማድረግ፡፡
እዚህ ጋር በቅርብ ዓመታት ከተሰሩ የሙዚቃ ስራዎች ውስጥ የተመስገን
ገብረእግዚአብሔርን የሙዚቃ ስራ እንጥቀስ፡፡ ሙዚቃው “ሐና” ይሰኛል፡፡
ልጠይቅሽ ብዬ ደጋግሜ ስልኩን
ብሞክርም
አድራሻሽን አጥቶ ይባክንልሻል ልቤ
አሁንም
ነግቶ ላይሽ ብየ ስነሳም
ብደውልም ስልክሽ አይነሳም…፡፡
ስልክ በታሪክ ሂደት ያለፈበት መንገድ ከሰዎች ጋር የነበረውና ያለው ቁርኝት በራሱ አዝናኝና አስገራሚ ነገር ነው። ከዚህም ባለፈ ስልክ በራሱ በግጥም፣ በስዕልና በሙዚቃ የተገለጸ እና ለኪነ ጥበብ እድገት የራሱን አሻራ ያኖረ ነው፡፡ በአማርኛ እና እንግሊዝኛ ፊልሞች ላይም ደጋግመው ከሚታዩ ትዕይንቶች ውስጥ አንዱ ስልክ ነው፡፡ በተለያዩ የሙዚቃ ስራዎችም ስልክ፣ ከናፍቆት፣ ከፍቅርና በርቀት ያሉ ሰዎች እንዳይረሳሱና እንዳይነፋፈቁ የሚያደርግ ከሰው ልጅ ህይወት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
እዚህ ላይ በአማርኛ እና አፋን ኦሮሞ የተሰራውን የድምጻዊት ፍሬህይወት ግርማ “ሄሎ” የተሰኘ ዘፈን መጥቀስ እንችላለን፡፡ በተለይ ይህ ሙዚቃ በስደትና ፍቅር መካከል ስልክ ያለውን ሚና የሚያሳይ ነው ማለት እንችላለን፡፡
ሁሌ እመጣለሁ ብሎ በሃሳብ
ኑሮ አንድ ቀን እንኳን ሳይሞላ
እኔም እንደወጣሁ ቀረሁ
ናፍቆት አንጀቴን እንደበላው
አንተስ እንደምን አለህ ሆዴ
ወገን እንዴት ነው ሰፈር ሃገሬ
ኑሮው አልሞላ ብሎኝ እንጅ
ልቤ እዛው ነው ቢርቅም እግሬ
በዛ አሳቤ በዛ ሃሳቤ
ሃሎው በለኝ እንጅ ምነው ሰጋ ልቤ…፡፡
ይህ ስልክ፣ ናፍቆትና ትዝታን ያጣመረው ዘፈን በዩቱብ ብቻ በርካታ ሚሊዮን ሰዎች አይተውታል፡፡ ስሜታቸውን ገልጸውበታል፡፡ አብዛኞቹ ሃሳቦች ስልክ ባይኖር ኖሮ እንኳን ከሀገሩ የወጣ አንድ ከተማ የሚኖረው ሰውስ እንዴት ይገናኝ ነበር የሚያስብል ነው፡፡
ራሳል ሆሳይን የተባሉ ምሁር እ.ኤ.አ. በ2022 “A Short Review on the History of Mobile Phones” በሚል ባስነበቡት ጹሑፍ ላይ እንደገለጹት ስልክ በተለይ ሞባይል በሰዎች የዕለት ተዕለት ተዝናኖት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ቁስ ነው፡፡
ቀደምት የሞባይል ስልኮች ዋነኛ ዓላማቸውና የተሰሩበት ምክንያት ከሰዎች ጋር ለመገናኘትና መልዕክት ለመለዋወጥ ነበር፡፡ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ የእጅ ስልኮች መፈጠርን ተከትሎ እንደ ጌሞች (ጨዋታ) እና ካሜራ ያሉ የመዝናኛ አማራጮችን አካትተው መጡ፡፡ ይህም በአሁኑ ጊዜ የምናያቸው ስማርት ፎኖች እንዲፈጠሩ አድርጓል። እነዚህ ደግሞ በርካታ የመዝናኛ አማራጮችን ለማግኘት የሚያስችሉና እጅግ ተመራጭ ሆነዋል፡፡ በዚህም ስልክ እየተዘፈነለትም ፣ ሙዚቃ እየታየበትና እየተሰማበትም ወሳኙ የህይወት አካል ሆኖ ቀጥሏል፡፡
በጊዜው አማረ