የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማምረት የላቀ ሚና እየተወጡ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

You are currently viewing የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማምረት የላቀ ሚና እየተወጡ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

AMN- ሰኔ 07/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ የተዘጋጀው 15ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፍቷል።

ከሰኔ 7 እስከ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄደው 15ተኛው ዙር የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ”ብሩህ አእምሮዎች በህሎት የበቁ ዜጎች ” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ስለመሆኑ በኤግዚቢሽን መርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ ተገልጿል።

ኤግዚቢሽኑን መርቀው የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባደረጉት ንግግር ለዘመናት በእንቅልፍ ውስጥ የቆየችው አዲስ አበባ ከተማ አሁን ላይ ነቅታ በርካታ ለውጦችን እያስመዘገበች ነው ብለዋል።

የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተሰጣቸው ተልዕኮ በየትኛውም ተቋም ሊተካ የማይችል ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማምረትና በክህሎት የበቁ ባለሙያዎችን በማፍራት የላቀ ሚና እየተወጡ ነው ብለዋል።

ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተመርቃችሁ የወጣችሁ ዜጎች ሀገራችንን መለወጥና ማሳደግ እንችላለን ብላችሁ በትጋት ልትሰሩ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው በከተማዋ በ15 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በአጠቃላይ ከ300 ሺህ በላይ በአጫጭርና ከ40 ሺህ በላይ በመደበኛ መርሃ ግብር ሰልጣኞችን መቀበልና ማብቃት ችለናል ብለዋል።

በየዓመቱ የሚከበረው የቴክኒክና ሙያ ሳምንትም አላማው የህብረተሰቡን የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት እንደሆነ ተናግረዋል።

ለአምስት ቀናት ለህዝብ ክፍት ሆኖ በሚቆየው የቴክኒክና ሙያ አውደ ርዕይ ላይ የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ የፖናል ውይይቶች የጥናት እና ምርምር ስራዎች ይቀርባሉ።

በአውደ ርዕዩ ላይ በ15 የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ውስጥ የተሰሩ ከ150 በላይ የቴክኖሎጂ ስራዎች ቀርበዋል።

ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ከ70 በላይ ተግባራዊ የሆኑ ምርምሮችም በአውደ ርዕዩ የተካተቱ ሲሆን በኮሌጆች መካከል ውድድሮች እንደሚካሄዱም ከወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።

በምትኩ ተሾመ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review