AMN- ግንቦት 25 /2018 ዓ/ም
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ያሳዩት ከፍተኛ የዲሞክራሲ ንቃተ-ህሊና እና ጽናት በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚገልጥ ነው፡፡
ድምፃቸውን ለመስጠት በማለዳው የተሰለፉ ዜጎች ፣ እስከ እኩለ ለሊት በትዕግስት ጠብቀው ድምፅ መስጠታቸው የከተማዋን ነዋሪዎች ለዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳየ ነበር።
በናንትናው ዕለት በሁሉም የከተማዋ ማዕዘናት የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ለዴሞክራሲ ግንባታ የራስን አሻራ ለማስቀመጥ ረጅም ሰልፎችን አስተናግደዋል፡፡
ህጻናትን ያቀፉ እናቶች፣ አረጋውያን፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ ዲሞክራሲያዊ መብታቸው ለመጠቀምና እና የሀገራቸውን የቀጣይ አምስት አመት መሪ ለመምረጥ በምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፃቸውን ሰጥተዋል ፡፡

የቀኑ ብርሃን አልፎ የምሽቱ ቅዝቃዜ ቢተካም፣ በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች የነበሩት ረጅም ሰልፎች አልቀነሱም ነበር፡፡ ከንጋት 9 ሰዓት ጀምሮ ነዋሪዎች እስከ እኩለ ለሊት 7 ሰዓት እና ከዚያም በላይ መራጮች በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው በፅናት ቆመው ድምፅ ሰጥተዋል፡፡
ይህ ሂደት በተለይ በዲጂታል ሚዲያና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ሰፊ መነጋገሪያና አድናቆትን ያተረፈ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ ረጅሙን የጥበቃ ሰዓት ተከትሎ በዜጎች መካከል የታየው መረዳዳትና አብሮነት የምርጫውን ሂደት ይበልጥ ውብ አድርጎታል፡፡ ወጣቶች ለአረጋውያን፣ ለነፍሰ ጡር እናቶችና ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ በመስጠትና መቀመጫዎችን በማመቻቸት አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪዎችና በጎ ፈቃደኞች በሰልፍ ላይ ለነበሩ ዜጎችና ለምርጫ አስፈጻሚዎች ውሃና ቀላል ምግቦችን በማቅረብ ታሪካዊ አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡
ይህ የነዋሪዎች ጽናት የሚያሳየው ህዝቡ ምርጫን እንደ አንድ ክንውን ሳይሆን የሀገርን የፖለቲካ ሽግግርና የዲሞክራሲ ጉዞ ለማፅናት ያለባቸውን የዜግነት ሃላፊነትና የባለቤትነት ማረጋገጫ አድርጎ መመልከቱን ነው፡፡
እስከ እኩለ ለሊት የዘለቀው ሰልፍና የታየው ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ ለቀጣይ የሀገሪቱ የዲሞክራሲ ጉዞዎችና ተቋማዊ ግንባታዎች ትልቅ ስንቅና መማሪያ የሚሆን ታሪካዊ እሴት ጥሎ አልፏል፡፡
በፍሬሕይወት ብርሃኑ