ባለፉት ዓመታት በመንግስት በኩል ለቱሪዝም ዘርፉ በተሰጠ ትኩረት ክልሉን የሀገር ውስጥ እና የዉጭ ቱሪስቶች መዳረሻ ማድረግ መቻሉን የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ገልጿል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የቱሪስት የመስህብ ስፍራዎችን ማስተዋወቅ አላማው ያደረገ የመገናኛ ብዙሃን ልዑክ በኦሮሚያ ክልል ጉብኝት እያደረገ ነው፡፡
በርካታ የቱሪስት የመስህብ ማዕከላትን በጉያው ያቀፈው የኦሮሚያ ክልል፣ ባለፉት ዓመታት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ምርጫ እና መዳረሻ መሆኑ ተገልጿ፡፡
በኦሮሚያ ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት እና ፕሮሞሽን ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ፋንታሁን ታደሰ ለኤ ኤም ኤን እንደገለፁት፣ በክልሉ ባለፋት ዓመታት የቱሪዝም ሀብቶችን ከመሰረተ ልማት ጋር የተሰናሰሉ እንዲሆኑ መሰራቱ፣ ዘርፉ እንዲነቃቃ ሀብቶቹንም የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
የአሁኑ ጉብኝትም የክልሉን የቱሪዝም ፀጋዎች ለሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ማስተዋወቅ እንዲሁም ባለፉት ዓመታት ለቱሪዝም ዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ግንዛቤ ለመፍጠር ዓላማ ያነገበ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በጉብኝቱ በርካታ የክልሉ የቱሪዝም ሀብቶች የሚቃኙ ሲሆን፣ በዛሬው እለትም በምዕራብ አርሲ ዞን የሚገኙት አብያታ-ሻላ ሀይቆች ብሔራዊ ፓርክ እና በዙሪያው ያሉ ፀጋዎች ተጎብኝተዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ታዋቂ ግለሰቦች እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በመጎብኘት ላይ ይጋኛሉ፡፡
በተመስገን ይመር