AMN – ነሐሴ 8/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ የፀረ-ሙስና ትግል የሕዝብና የመንግሥት ዘላቂና ዋና አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለጹ።
የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል ማጠቃለያ መድረክ “የፀረ-ሙስና ትግል ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፤ ዛሬ የምናከብረው የጸረ-ሙስና ትግል ያለፈውን ለመዘከር ብቻ ሳይሆን፣ ያለንበትን ለመገምገምና ወደፊት የምንመራበትን አቅጣጫ ለመወሰን የሚያስችለን ነው ብለዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዋና መወያያ ነጥቦች መካከል ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በግንባር ቀደምትነት የተቀመጠ አጀንዳ መሆኑን አንስተው፤ የፀረ-ሙስና ትግሉ የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የመላው ህዝብ የጋራ ሀገራዊ ህልውና ጉዳይ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ባለፉት 25 ዓመታት ኮሚሽኑ በሦስት ዋና ዋና የትግል ስልት ላይ ተመስርቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ያስታወሱት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፤ የዜጎችን አስተሳሰብ የሚቀርፅ የሥነ-ምግባር ግንባታ፣ የሌብነት ቀዳዳዎችን የሚደፍን የሙስና ቅድመ-መከላከል፣ እና ጥፋተኞችን ለፍትህ የሚያቀርብ የህግ ማስከበር ስራዎች ናቸው ብለዋል።
እነዚህ ሦስት መሰረቶች የፀረ-ሙስና ትግሉ የማዕዘን ድንጋዮች ሆነው አሁንም ያገለግላሉ ሲሉ አስታውቀዋል።
ኮሚሽኑ በ25 ዓመታት የሥራ ጉዞው በሥነ-ምግባር ግንባታ፣ በሙስና መከላከል፣ የሕዝብ ግንዛቤን በማሳደግ፣ በተቋማት የፀረ-ሙስና አቅም ማጠናከርና በተጠያቂነት ሥርዓት ዝርጋታ ከሁሉ በላይ ሙስናን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ከማፍጠር አንፃር በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት መንግስት ሙስናን ለመታገል ዘመናዊ እና መዋቅራዊ የሪፎርም ስራዎችን በስፋት እየተገበረ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በተለይም ሀገራዊ የጥቆማ መቀበያ ሥርዓት፣ የዜጎችን ድምፅ ያለስጋት እንዲሰማ አድርጓል ብለዋል።
ዲጂታል የሀብት ማሳወቂያ እና ማስመዘገቢያ ሥርዓት ደግሞ የመንግስት ተቋማት አመራር እና ሰራተኞች ሀብት ለህዝብ ግልጽ መደረጉን ያነሱት አፈ ጉባኤዋ፤ በመሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎትና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የተደገፉ አሰራሮች ሌብነትን በቴክኖሎጂ አቅም የሚያጋልጡ አዲስ የትግል ምዕራፎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ሙስና የገንዘብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሥነ-ምግባር፣ የሞራል፣ የአስተዳደር፣ የፍትሕ፣ የልማት፣ የሀገር እና የትውልድ ግንባታ ጉዳይ በመሆኑ ሁሌም ቋሚ የህዝብና የመንግሥት አጀንዳ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚገባም ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።