ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 989 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡
ዩኒቨርስቲው በቅድመ ምረቃ በተለያዩ ዘርፎች ወንድ 603፣ ሴት 670 በድምሩ 1 ሺህ 273፣በማስተርስ ዲግሪ ወንድ 480 ሴት፣ 226 በድምሩ 706፣ እንዲሁም የመጀመሪያዎቹን የዶክተሬት ዲግሪ (ፒ ኤች ዲ) ምሩቃን ወንድ፣ 5 ሴት 1 በድምሩ 6፣ በአጠቃላይ 1 ሺህ 989 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ሰዓት በአካዳሚኩ ዘርፍ በ31 የቅድመ-ምረቃ፣ በ33 የድህረ-ምረቃ እና በ6 የፒ ኤች ዲ ፕሮግራሞች ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ የዪንቨርስቲው ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ማሻሻልን ተልዕኮው አድርጎ አዲስ አወቃቀር፣ ተልዕኮና ተጠሪነትን ያነገበው አንጋፋው ዩኒቨርሲቲ፣ በረጅሙ ታሪካዊ ጉዞው ሀገሪቱ የምትፈልገውን የተማረ የሰው ኃይል ፍላጎት በማሟላት ረገድ የዘንድሮውን ተመራቂዎች ጨምሮ ከ120 ሺህ በላይ ባለሞያዎችን እና አንቱታን ያተረፉ ምሁራንን ማፍራቱንም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
አንጋፋው የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ፣ እድሜ ጠገብ የሆነውን ያክል ያላደገ፣ ተዘንግቶም የቆየ በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት ይህንን አሮጌ ገፅታውን የሚያድስ ስር ነቀል ለውጥ በማድረግ ስያሜውን የሚመጥን ተቋም ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
ከፌዴራል፣ ከክልል እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት ተጨባጭ ለውጦችን እያስመዘገበ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በጥቅሉ በዚህ ዓመት በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መሰራቱንም ጠቅሰዋል።
በታምራት ቢሻው