በደም የተፃፈ ገድል

You are currently viewing በደም የተፃፈ ገድል

AMN- ሰኔ 16/2017 ዓ.ም

ወይዘሮ አሰጋሽ ጎሳ ይባላሉ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ የትምህርት እና ቅስቀሳ ባለሞያ ናቸው፡፡

ለ121 ጊዜ ደም በመለገስ የራሳቸውን ታሪክ ፅፈዋል፡፡

ዛሬ ላይ ለ121ኛ ጊዜ ደም ለመለገስ ምክኒያት የሆናቸውን አጋጣሚ እንዲህ ያስታውሱታል፡፡

በደም ባንክ ባለሞያ ሆነው እየሰሩ በነበረበት ወቅት ከክፍለ ሃገር በወሊድ ምክኒያት ደም እየፈሰሳት ጥቁር አንበሳ ለህክምና ባለቤቱን ይዞ የመጣ አባወራ፣ ከሆስፒታሉ ቁልቁል አየሮጠ በመምጣት የልጆቼ እናት ልትሞትብኝ ስለሆነ እሷ ከምትሞት እኔ ልሙት ደም መስጠት የሚገል እንኳን ቢሆን እሷ ከምትሞት እኔ ልሙት ብሎ እንደጠየቃቸው ያወሳሉ፡፡

ታዲያ ያኔ ውስጣቸው ባለመቻሉ ያንተን ፋንታ እኔ እሰጣለሁ በማለት የመጀመሪያውን ልገሳ እንዳደረጉ አጫውተውናል፡፡

በ1984 ዓ.ም በዚህ አንድ አጋጣሚ የተጀመረው የደም ልገሳ የበጎ ፍቃድ ተግባርም፣ ሶስት አስርት ዓመታትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል፤ ደም የሚያስፈልጋቸው ወገኖች እስካሉ ድረስም ደም ከመለገስ የሚያግደኝ ነገር የለም ይላሉ፡፡

የደም ልገሳ በቤተሰባቸውም የተለመደ ቅዱስ ተግባር መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ አሰጋሽ፣ ቤታቸው ሆስፒታል አካባቢ በመሆኑ፣ ወላጅ እናታቸውም ደም የተቸገሩ ወገኖች ሲያወሩ ሰምተው ምንም ግንዛቤ ባልነበረበት ወቅት እንኳን ደም እንደለገሱ ያስታውሳሉ፡፡

ታዲያ ይህንን ደም የመለገስ በጎ ተግባር የሚያሳዩ የተነሷቸውን ፎቶ ግራፎች የተመለከቱ ሰዎችም ይህንን ያክል ጊዜ ደም ስትለግሽ እኛ የት ነበርን የሚሉ እንዳሉም ነው የሚገልጹት፡፡

ለ121 ጊዜ ደም እየለገስኩ ነው እግዚአብሄር ይመስገን በጣም ጤነኛ ነኝ፤ ይህንን በማድረጌ ደስ ይለኛል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ሌሎች ቤተሰቦቼም ደም እየለገሱ ይገኛሉ ያሉት ወይዘሮ አሰጋሽ፣ ይህንን ተግባርም የሚቃወም እንደሌለ ያስረዳሉ፡፡

እርሳቸው ደም የሚለግሱት ሰው ለሶስት ሰዎች እንደሚደርስ በማንሳትም፣ ለ121 ጊዜ ደም በመስጠታቸው ለ363 ሰዎች መድረስ እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡

የሚያደርጉት የበጎ ፍቃድ ተግባርም ደስታን እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

በዚህ የተቀደሰ ደም የመለገስ ተግባር በመሳተፋቸውም የስራ ባልደረቦቻቸው እንደሚያበረታቷቸው የገለጹት ወይዘሮ አሰጋሽ፣ ኬክ በማዘጋጀት እና በማበረታታት ለሚያሳዩአቸው አብሮነትም አመስግነዋል፡፡

ደም መለገስ ጉዳት እንደሌለው በመግለጽም፣ ከመቀበል መስጠት ይሻላልና እኛ እያለን ማንም ሰው በደም እጦት መሞት የለበትም ብለዋል፡፡

ሁሌም ማሰብ የሚገባው ደም የሚያስፈልገው ከቤተሰቤ አንዱ ቢሆንስ የሚለውን እንደሆነ በማስገንዘብም፣ ደም ለመለገስ መስፈርቱን የሚያሟላ ማንኛውም ሰው ደም ሊለግስ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review