AMN — ግንቦት 4/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራን የሚፈጥሩ ወጣቶች ስራ እየተበራከተ መምጣቱ ማህበረሰቡ በፈጠራ ውጤቶቹ እየተጠቀመባቸው ይገኛል።
ኤ ኤም ኤን ያለነዳጅ የሚሰራ ጀነሬተር ከፈጠሩ ወጣቶች አንዱ ከሆነው ወጣት ሄኖክ አማኑኤል ጋር ቆይታ አድርጓል።
በኤሌክትሪካል ኢንስታሌሽን ሙያ ትምህርቱን እንደተከታተለ የሚገልጸው ወጣቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀው የቴክኖልጂ የፈጠራ ውድድር ላይ በመሳተፍ ባስመዘገበው ውጤት የተሻለ ክህሎት እንዲያገኝ ወደ ቻይና በመሄድ ተጨማሪ ትምህርት በመማር ያለውን ዕውቀት በማጎልበት ወደ ሀገሩ ተመልሷል።
ከጓደኛው ጋር በመሆን ያለቸውን ዕውቀት በመጠቀም መንግስት ያመቻቸላቸውን ዕድል በመጠቀም ያለ ነዳጅ በኤሌክትሪክ ቻርጅ እና በሶላር የሚሰራ ጀነኔተር መፍጠር እንደቻሉ ሄኖክ ለኤ ኤም ኤን ገልጿል።
ይሁን እንጂ ጀነሬተርን ከሰሩ በኋላ ተቀባይነቱ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ተቀባይነት ለማግኘት ለሁለት ዓመታት ያህል እንደፈጀባቸው ነው ወጣት ሄኖክ የሚገልጸው።
መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍ ዛሬ ላይ ምርታቸውን ለተለያዩ ተቋማት እና ግለሰቦች ተደራሽ በማድረግ ለገበያ እያቀረቡ ስለመሆኑ ተናግሯል ።
ጀነሬተሮቹ የተለያዩ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችሉ ሆነው የተሰሩ መሆናቸውን የሚናገረው ወጣቱ አንዴ ጊዜ ለሁለት ሰአት ቻርጅ በማድረግ ለረጅም ጊዜ መጠቀም የሚያስችሉ ሆነው የተሰሩ መሆናቸውን ገልጿል።
ያለነዳጅ የሚሰራ ጀነሬተር በአሁኑ ወቅት ተፈላጊነቱ እያደገ መምጣቱን የሚገልፀው ሄኖክ በኤሌክትሪክ ያለምንም ድምፅ የሚሰራው ጀነሬተር አረንጎዴ ኢኮኖሚን በመገንባት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልፆ በየትኛውም ቦታ በቀላሉ መገልገል የሚያስችል ስለመሆኑ ለኤ ኤም ኤን ተናግሯል።
በመሀመድኑር ዓሊ