የጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ የኖረ የኢትዮጵያዊ መከባበርና ትስስርን ተቋማዊ በሆነ መልኩ ያደራጀ መርሐ-ግብር መሆኑን የሰላም ሚኒስትሩ መሀመድ እንድሪስ ተናገሩ።
የጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ ሀገር አቀፍ የልምድ ልውውጥ መድረክ እየተካሄደ ነው።
የቃል ኪዳን ቤተሰብ ተማሪዎች እውቀት ለመቅሰም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲመጡ ለአካባቢው እንግዳ እንዳይሆኑ እና ከማህበረሰቡ ጋር እንዲተሳሰሩ ለማድረግ በጎንደር ከተማ ካሉ ቤተሰቦች ጋር የማስተሳሰር ተግባር ነው።
ሚኒስትሩ ጎንደር ከሌላ ቦታ የመጣውን ሰው እንግድነት እንዳይሰማው በፍቅር ማስተናገድ እንዲሁም ልጆቹን በአብሮነት እና ሀገርን በመውደድ ጠንካራ ስርዓት ውስጥ የሚያሳድግ ማህበረሰብ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህ መንገድ ቤተሰብ ለቤተሰብ እንዲሁም እንደ ማህበረሰብ ትስስርን በማጠናከር ኢትዮጵያ የምትሰራበት መንገድ መሆኑንም አቶ መሀመድ አብራርተዋል።

በሌላ መልኩ መርሐ-ግብሩ የትምህርት ጥራት እና የተማሪዎች ውጤት ላይ ያለውን መልካም ሁኔታዎችን በመረዳት ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮውን እንዲያስፋፉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲም ለወሰደው ኃላፊነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በፕሮግራሙ የማንነት እና ሌሎች ልዩነት ከግምት ባልገባ መልኩ የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት እንዲሁም እንዱ የኢትዮጵያዊያን የመጋመድ ልክ አንዱ ለሌላው ደጀን ያሳየንበት መድረክ ነው ብለዋል።
ፕሮግራሙ በተማሪዎች ውጤት እና ተቋሙን ከህዝብ ጋር ከማስተሳሰር አንፃርም ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እያንዳንዱ ዩኒቨርስቲም ለሀገር በቀል እውቀቶቻችን በሰጡት ትኩረቶች ልክ አንድነታችን አየጠነከረ ይሄዳልም ነው ያሉት።
የሰላም ሚኒስቴር ባዘጋጀው መድረክ ላይ የተለዩ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የሀለያዩ ከተማ አስተዳደሮች የስራ ኃላፊዎች፣ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎችም እየተሳተፉ ነው።
በአፈወርቅ አለሙ