AMN-ነሐሴ 02/2018ዓ.ም

በኦሮሚያ ክልል በግብርና እና በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የተመዘገበው ስኬት የክልሉን ገቢ በከፍተኛ መጠን እንዲያድግ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናግረዋል።
የክልሉ ገቢ በ2010 ዓ.ም 13.8 ቢሊዮን ብር ከነበረበት አሁን ወደ 342 ቢሊዮን ብር ማሳደግ መቻሉንም ጠቅላይ ሚንስትሩ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል።
ይህ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የገቢ ዕድገት ሊመዘገብ የቻለው የሕዝቡ ንቃተ ሕሊና በማደጉ፣ አስተሳሰቡ በመስፋቱ እና በየዘርፉ የተከናወኑት ሥራዎች ውጤታማ በመሆናቸው እንደሆነ አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በቃለ ምልልሳቸው ፣ በኦሮሚያ ክልል የሕዝቡን የኢኮኖሚ ፍላጎቶችን ለመመለስ በተሠራው ሥራ ሕዝቡ ያለውን የመሬት እና የሀብት አቅም ተጠቅሞ እንዴት እየተለወጠ እንደሚገኝ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው፣ የኢኮኖሚ ጥያቄ የሕዝቡ ዋና ጥያቄ እንደነበር አስታውሰው፣ አርሶ አደሩ በላቡ ያገኘውን ፍሬ የሚበላበትን መንገድ ማመቻቸት ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ እና አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ከለውጡ በፊት በኦሮሚያ ክልል የሚታረሰው መሬት 6.6 ሚሊዮን ሔክታር ገደማ እንደነበር እና በአሁኑ ወቅት ግን የበጋ መስኖ ልማትን በስፋት በመጠቀም፣ በአዲስ መልክ በክላስተር በማደራጀት እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን በማሳተፍ የሚታረሰው መሬት መጠን ወደ 17 ሚሊዮን ሔክታር ማደጉን ጠቁመዋል።
ይህ የመሬት አጠቃቀም ዕድገት በምርት መጠን ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን አስረድተዋል።
በ2010 ዓ.ም በበጋ እና በክረምት ወቅት የተመረተው አጠቃላይ የምርት መጠን 163 ሚሊዮን ኩንታል ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ባለፈው ዓመት የተሰበሰበው አጠቃላይ ምርት ወደ 550 ሚሊዮን ኩንታል አድጓል ብለዋል።
ላለፉት 100 ዓመታት በላይ ሲታረስ የነበረው መሬት 163 ሚሊዮን ኩንታል ሲያመርት፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ምርቱን ወደ 550 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ መቻሉ ትልቅ ታሪክ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል ቀደም ሲል ባለሀብቶች የእርሻ መሬት ወስደው የአካባቢውን ሕዝብ ጥቅም ሳያከብሩ የመንቀሳቀስ አሠራር እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ላይ ያ አሠራር መቅረቱን አስረድተዋል።