በኦሮሚያ ክልል ተስፋ ሰጪ ለውጦች ተመዝገበዋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ነሐሴ 1/2018 ዓ.ም

በኦሮሚያ ክልል በሁሉም ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ጋር ባደረጉት ቆይታ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በኦሮሚያ ክልል በግብርና፣ በገቢ እና በበጀት እድገት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በሁሉም ዘርፎች እየመጣ ያለው ለውጥ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

በግብርናው ዘርፍ የታየውን ለውጥ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከለውጡ ወዲህ በክልሉ በግብርና ስራ የተሸፈነው መሬት ከ6 ሚሊየን ሄክታር ወደ 17 ሚሊየን ሄክታር ማደጉን ተናግረዋል።

በዚህም ባለፈው ዓመት አጠቃላይ ምርታማነትን በማሳደግ 500 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት መቻሉን ጠቁመው፤ ቀሪ ስራ ቢኖርም በርካታ አዎንታዊ ውጤቶች መጥተዋል ብለዋል።

የክልሉን የገቢና የበጀት እድገት አስመልከተው ሲናገሩም፤ በ2010 ዓ.ም የነበረው የክልሉ ገቢ ከነበረበት 13 ቢሊየን ብር በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ወደ 342 ቢሊየን ብር ማደጉን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በ2010 ዓ.ም 52 ቢሊየን ብር የነበረው የክልሉ አጠቃላይ በጀት በዘንድሮው ዓመት 700 ቢሊየን ብር መድረሱን አስረድተዋል።

የሀብት ማደግ የህዝብን ተጠቃሚነት በቀጥታ እንደሚያሳድግ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም በከተሞች ልማት በኩል ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።

ለአብነትም በቢሾፍቱ፣ በአዳማ፣ በጅማ፣ በሮቤ እና በሌሎች ከተሞች የታየው እንቅስቃሴ የዚሁ ትልቅ ለውጥ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review