የምርምርና የቴክኖሎጂ ልማትን በማስፋፋት የግብዓት አቅርቦትን በራስ አቅም ማሳደግ ይገባል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

AMN- ነሐሴ 1/2018 ዓ.ም

የምርምርና የቴክኖሎጂ ልማትን በማስፋፋት እና የዲጂታላይዜሽን ስራዎችን በማጠናከር የግብዓት አቅርቦትን በራስ አቅም ማሳደግ ይገባል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አሳስበዋል፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ስር እየተካሄዱ ያሉ የአዳማ ጋርመንትና ኢንዱስትሪ፣ የጋሻ የሠራዊቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት እና የመከላከያ ባጅና ሜዳሊያ ማምረቻ ፋብሪካን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የአዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ ያስገነባውን አዲስ የማስፋፊያና የማሻሻያ ፕሮጀክት በይፋ መርቀው ከፍተዋል።

በጋሻ መኖሪያ ፕሮጀክት፣ በአዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ እንዲሁም በመከላከያ ባጅና ሜዳሊያ ማምረቻ ፋብሪካ የተከናወኑ የልማት ስራዎችንም ተመልክተዋል፡፡

በወቅቱ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ያስመዘገበውን አስደናቂ ለውጥ ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

የፋውንዴሽኑን አመራሮችና ሰራተኞች ላስመዘገቡት ውጤት አመስግነው የተገኘው ለውጥ ሳያዘናጋቸው ለበለጠ ውጤት እንዲተጉ አሳስበዋል።

በቀጣይም የምርት ጥራትን በማሻሻል፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ልማትን በማስፋፋት፣ የዲጂታላይዜሽን ስራዎችን በማጠናከር፣ የግብዓት አቅርቦትን በራስ አቅም በማሳደግ በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪ እንዲገነባ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

“ሰራዊቱ መለኪያው ሀገሩ ነው” ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የመከላከያ ሰራዊት ፋውንዴሽን የተቋሙንና የሀገሪቱን ፍላጎት በማሳካት ያለውን ሚና ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባው መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በጉብኝቱ ላይ የአዳማ ከተማ የሥራ ሃላፊዎችን ጨምሮ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የፋውንዴሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review