የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ሀገር ግንባታና ህልውና ውስጥ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ነሐሴ 1/2018 ዓ.ም

የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ሀገር ግንባታና ህልውና ውስጥ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የነበረውንና ያለውን ታሪካዊ ሚና ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኦሮሞ ኢትዮጵያ ነው፤ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ አይገነጠልም ሲሉ ገልጸው፤ የኦሮሞ ህዝብ ወዴት እንደሚያመራ ሳይታወቅ በሚነሱ የመገንጠል ሀሳቦች ምክንያት ህዝቡ እንዲገለል ተደርጎ መቆየቱን ጠቁመዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ያልተሳተፈበት ምንም አይነት ታሪካዊ ክስተት እንደሌለና በኢትዮጵያ ግንባታ ታሪክ ውስጥ አንዴም ወደ ኋላ ብሎ እንደማያውቅ ነው የተናገሩት።

በሀገር ድንበር ማስከበር እና በጦር ሰራዊት ግንባታ ሂደት የኦሮሞ ተወላጆች ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመን የኢትዮጵያን ዘመናዊ ድንበር ካሰመሩት ዋና ዋና ሰዎች አንዱ ራስ ጎበና ዳጬ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ዘመናዊ ሰራዊት ከመገንባት አንጻር የአባ መላ (ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ) እንዲሁም በቅርብ ባለው ጊዜ የጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ አስተዋጽኦ ታላቅ እንደነበር ገልጸዋል።’

በተጨማሪም የኦሮሞ ጀግኖች በዓድዋ፣ በማይጨው እና በባድመ ጦርነቶች ያበረከቱት አስተዋጽኦ የታወቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዓድዋ ድል ውስጥ በርካታ የኦሮሞ ተወላጅ ጀግኖች ታላቅ ስራ መስራታቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ግንባታ ውስጥ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ማሳነስ ከሀቅ ጋር መጣላት መሆኑን አስገንዝበዋል።

በዘመናዊ ቢሮክራሲ፣ ኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ትግል በኩል የነበረውን አስተዋጽኦ ሲያብራሩም፣ የሀገሪቱን የኢኮኖሚና የዘመናዊ ቢሮክራሲ መዋቅር በመገንባት በኩል አቶ ይልማ ደሬሳን በአብነት ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ መሬት ላራሹ በሚለው የተማሪዎች እንቅስቃሴ እና በፖለቲካው የትግል ጉዞ ውስጥ የሀይሌ ፊዳ እና የባሮ ቱምሳ ሚና ከፍተኛ እንደነበር አብራርተዋል።

የኦሮሞ ህዝብ የትግል ጉዞ እዚህ የደረሰው በቅብብሎሽ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከለውጡ ወዲህ የህዝቡ የትግል ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸውን አስረድተዋል።

አሁን ላይ ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ፣ ወደ ፊት ወይም ወደ ኋላ መመልከት እንደማያስፈልግና ኦሮሞ ሙሉ በሙሉ ነጻ መውጣቱን ተናግረዋል።

አሁን መቶ በመቶ ኦሮሞ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ጀምሯል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህል፣ የማንነት ጥያቄዎች ዛሬ ጥያቄ አይደሉም ብለዋል።

በሂደት ደግሞ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ዘመኑን የሚመጥኑ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review