የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየሠራን የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤን ለማስተናገድ ተዘጋጅተናል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን 2ኛውን የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የጋዜጣዊ መግለጫው ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በጀመረቻቸው ጥረቶች በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል፤ለላቀ ስኬትም ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
በዚህወሳኝ ወቅት ኢትዮጵያ ከጣልያን መንግሥት እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመቀናጀት 2ኛዉን የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤ እንድታዘጋጅ ተመርጣለች፡፡
ይህም በኹለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ግንኙነቶች ውስጥ ኢትዮጵያ እየተጫወተች ያለዉን ሚና የሚጎላ፣ በሥርዐተ ምግብ ዙሪያ የጀመረቻቸዉን ስኬታማ ተግባራት የሚያበረታታ ነው፡፡
ከዐራት ዓመታት በፊት በመጀመሪያዉ የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ኢትዮጵያ በምታስተናግደዉ መድረክ ይገመገማል፤ ቀጣይ አቅጣጫዎችም ይቀመጣሉ፡፡
ኢትዮጵያ በምታስተናግደዉ ጉባኤ ርኃብን ስለማስወገድ እና ምግብ ዋስትና፣ስለ አየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶች ምክክር ይደረጋል፤ ቀጣይ መወሰድ የሚገባቸዉ ርምጃዎችም ይመላከታሉ፡፡
ኢትዮጵያ ጉባኤዉን የምታስተናግደዉ ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን በማስመዝገብ የማንሰራራት ጉዞን በጀመረችበት ወቅት ነው፡፡
ለጉባኤዉ በተሞክሮነት የምታካፍላቸዉ በርካታ ስኬቶችም አሏት፡፡
በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ ስኬታማ ድሎችን አስመዝግባለች፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ረገድም ባለፉት በጣት የሚቆጠሩ ዓመታት ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ለዓለም አብነትናት፡፡
ጉባኤዉ በሚካሄድበት በዚህ ክረምትም 7.5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እየተጋች ነው፡፡
የሚተከሉት ችግኞች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከማስቻላቸውም በላይ የምግብ ዋስትናን እና ሥርዐተ ምግብን ለማሻሻል ሚና ያላቸው ናቸው፡፡
የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤን እንድታስተናግድ ለኢትዮጵያ ዕድል መሰጠቱም ይህንን ጅምር ዕውቅና የሚሰጥ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ባለብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ እየገነባች እና ኹለንተናዊ ስኬት እያስመዘገበች ባለችበት በዚህ ወቅት ከሐምሌ 20-22/2017 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ሥርዐት ጉባኤን በአዲስ አበባ ታስተናግዳለች፡፡
በጉባኤዉ የአገር መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ሳይንቲስቶች፣ የምግብ አምራቾች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ የሴቶች ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ይሳተፋሉ።
ኢትዮጵያም የመዲናዋን ገጽታ በእጅጉ ለውጣ እንግዶችን በላቀ ዝግጅት ለመቀበል ተሰናድታለች፡፡
በርካታ ስኬቶቿንም በልምድነት ለማካፈል ተዘጋጅታለች፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ለዘመናት ያስቀጠሉትን ለኹለትዮሽና ባለብዝኃ ወገን ግንኙነት ትኩረት የመስጠት ልምድ ተጠቅመዉ ጉባኤዉን በላቀ ስኬት ለማስተናገድ በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል፡፡
###
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት