የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሰሜን አሜሪካ እና ካናዳ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተወካዮች ምርጫ በቅርቡ ያካሂዳል

You are currently viewing የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሰሜን አሜሪካ እና ካናዳ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተወካዮች ምርጫ በቅርቡ ያካሂዳል

AMN ነሐሴ 16/2017

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሰሜን አሜሪካ እና ካናዳ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተወካዮች ምርጫን በቅርቡ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ በሰጡት መግለጫ፥ኮሚሽኑ አካታችነት እና አሳታፊነቱን በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም ከሀገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ተቋማት እና ማህበራትን በማሣተፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ እና በካናዳ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተወካዮች ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ሂደትም ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ተቋማት እና ማህበራት እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ ዳያስፖራ ወገኖችን በአካል እና በበይነ መረብ እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻችም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ለመሰብሰቢያ አዳራሽ እና ለሎጂስቲክስ ዝግጅት ይመች ዘንድ የምዝገባ ሂደት እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በሰሜን አሜሪካ የሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተወካዮች ምርጫ ነሐሴ 24 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚከናወን ጠቁመው፤ የካናዳውም የሰሜን አሜሪካውን ተከትሎ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆንም ሁሉም አካላት የነቃ ተሣትፎ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በህግ-ጥላ ስር የሚገኙ ዜጎችን በሀገራዊ ምክክሩ ለማሣተፍ ከፍትህ ሚኒስቴር እና ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በጎ ምላሽ ተገኝቶ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በደቡብ አፍሪካ ያካሄደው የምክክር ሂደት በሁሉም መስኩ ውጤታማ እንደነበር አስታውሰዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review