AMN- ሰኔ 13/2018 ዓ.ም
በዲጂታል መሪነት እየተለወጠ ባለ ዓለም ውስጥ መልማት የሚቻለው የቴክኖሎጂ መሠረትን በማስፋት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ የተከፈተውን እና በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያ መጎብኘታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በፈጣን እና ተለዋዋጭ የዲጂታል ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ እና ቀጣይነት ያለው ልማት ማሳካት የምትችለው የተጀመረውን የዲጂታል ልማት በማሳደግ መሆኑን ጠቁመዋል።
አገልግሎት አሰጣጥን ፈጣን እና የተሳለጠ ማድረግ፣ በተቋማት የሚሰጥን አገልግሎት ማቀናጀት እንዲሁም ድካምን ማቅለል በቀጣይ የሚጠበቁ ሥራዎች መሆናቸውን ያነሱት አቶ ተመስገን ፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶች እና የተጣሉ መሠረቶች ለሀገራዊ ልማት ራዕይ መሳካት ትልቅ ጉልበትና መነሻ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የቴክኖሎጂ እና የዲጂታል አሠራሮችን ማሳደግ ለሀገሪቱ ብሔራዊ ዕድገት እና ለሰው ተኮር ልማት ጉዞ የማይናወጥ መሠረት እንደሚሆን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።