የጉልበት ብዝበዛ ወንጀል ሲፈፀምባቸው የነበሩ 18 ህፃናትና ታዳጊዎችን ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ፡፡
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው ኦ አቤም ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ የሰባት ዓመት ታዳጊ በመንገድ ላይ እያለቀሰ ሳለ ለምን እንደሚያለቅስ ሲጠየቅም ለስራ የተሰጠው ሚዛን እንደጠፋበትና አሰሪዎቹም ቤት እንደማያስገቡት ይናገራል።

የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከታዳጊው የተቀበለውን መረጃ መነሻ በማድረግና ተገቢውን ክትትል በማከናወን በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ቦታው ቻይና ካምፕ አካባቢ ከሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ዕድሜያቸው ከ7 እስከ 13 ዓመት የሆኑ 18 ህፃናትና ታዳጊዎችን ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ሊያውልም ችሏል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ እነዚህኑ ህፃናትና ታዳጊዎች ክልል ድረስ በመሄድ ከቤተሰቦቻቸው ላይ እናስተምራቸዋለን ብለው በማምጣት ቆሎ፣ ሶፍት እንዲሁም ሚዛን በማሰራት ከእያንዳንዳቸው በቀን ከ150 እስከ 300 ብር ገቢ እንዲያስገቡ ከማድረጋቸውም በላይ የወንጀል አፈጻጸሞችን (የመኪና ስፖኪዮ አነቃቀል) ያስተምሯቸው እንደነበርም የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

በግለሰቦቹ ላይ ተገቢው ምርመራ እየተደረገ ሲሆን በዐ/ህግም በኩልም ክስ እንደተመሠረተባቸው ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ሕፃናትን ለእድሜያቸው በማይመጥን የጤና፣ የእድገት፣ የማኅበራዊና ስነ-ልቦናዊ ደህንነታቸውን የሚጎዳና ለህይወታቸው አስጊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲሰሩ ማድረግ የህግ ተጠያቂነት የሚያስከትል ተግባር በመሆኑ ህብረተሰቡ መሰል ድርጊቶች ሲያጋጥሙት በአቅራቢያው ለሚገኝ የፀጥታ ተቋም መረጃ በመስጠት በህፃናት ላይ የሚደርስ የጉልበት ብዝበዛን መከላከል ይገባል ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡