የምክክር ጉባኤው ውጤታማ ሂደት ተስፋን የሚያለመልም ነው

You are currently viewing የምክክር ጉባኤው ውጤታማ ሂደት ተስፋን የሚያለመልም ነው

AMN ሐምሌ 29/2018

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ውጤታማ ሂደት ተስፋን የሚያለመልም መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲሱ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪሎችም በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛል።

የጉባኤው የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች እንደገለጹት፤ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምጾች የሚስተጋቡበት፣ አሳታፊና ግልጽ የመግባባት መድረክ ነው።

በተመካካሪዎች መካከልም አንዱ የሌላውን ሀሳብ የሚያዳምጥበትን ወርቃማ ዕድል በመፍጠር፣ የጋራ መግባባትን የሚገነባና ተስፋን የሚያለመልም ሂደት መሆኑን ገልጸዋል።

ተመካካሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የሚነሱ ሀገራዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት ለረጅም ዘመናት ግጭት፣ ኃይልና ተቃርኖ የተለመደ መንገድ ሆኖ ቆይቷል።

ምክክር አዋጭ የመፍትሔና የመግባባት መንገድ ነው ያሉት ተመካካሪው፤ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪሎች በአንድነት ስለ ሀገር የሚመክሩበት ዕድል መፈጠሩም አዲስ የሀሳብ ገበያ መከፈቱን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ የሀገር ግንባታ ባህልን ለማጎልበት አሻራችንን የምናኖርበት ዕድል መፈጠሩ ትልቅ ዕድልና ኃላፊነት ነው ብለዋል።

ሌላኛው ተመካካሪ አቶ ወንድሙ ግዛው በበኩላቸው፤ ጉባኤው ለቀጣዩ ትውልድ በሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ መግባባት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለማስረከብ መሠረት የሚጥል የሀሳብ ሜዳ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ውጤታማ ሂደትም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግርና ተስፋን የሚያለመልም መሆኑን ተናግረዋል።

ጉባኤው ኢትዮጵያ ለዘመናት ያሳለፈቻቸውን ፈተናዎች በምክክር በመፍታት በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መፍትሔና መግባባት ለመገንባት የማይተካ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።

በጉባኤው የሚመከርባቸው ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ጥልቅ፣ አሳታፊና ግልጽ ምክክር እየተደረገባቸው ነው ያሉት ደግሞ ሌላው ተመካካሪ አቶ ታመነ ኃይሉ ናቸው።

በምክክር ጉባኤው በግልጽነትና በአሳታፊነት የሚመነጩ ሀሳቦች በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት አወንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ተመካካሪ አቶ በላይነህ ዴንሳሞ በበኩላቸው፤ ከሚለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ጉዳዮች ይበልጣሉ፤ በምክክራችንም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና የሚያስፈልገውን ምቹ መደላደል ለመፍጠር እየመከርን ነው ብለዋል።

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የልዩነት ነጥቦችን ወደ የጋራ መግባባት በመቀየር፣ የተሻለች፣ ሰላማዊትና ብልጽግናዋ የተረጋገጠ ኢትዮጵያ ለመገንባት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑንም መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review