AMN — ሐምሌ 28/ 2018 ዓ.ም
የቴሌቪዥን ጣቢያው “ኮኔክቲንግ አፍሪካ” በተሰኘው ልዩ ፕሮግራሙ የኢትዮጵያን አገራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር የያዘ ዘገባ አቅርቧል። ዘገባው ኢትዮጵያ በኃይል፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በኢንፍራስትራክቸር እና በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፎች በሚደረጉ ዋና ዋና ኢንቨስትመንቶች አማካኝነት ኢኮኖሚዋን ለማስፋፋት የምታደርገውን ጥረት አጉልቶ አሳይቷል።
ዘገባው እንደጠቀሰው ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ምርጥ የቡና ዓይነቶች አንዱን በማምረት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የምትታወቅ መሆኗን ጠቅሶ አሁን ላይ እንደ ታዳሽ ኃይልን፣ ማዕድንን፣ ቱሪዝምን እና ግዙፍ የኢንፍራስትራክቸር ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ወደ አዳዲስ ስትራቴጂካዊ ዘርፎች በመግባት ሰፊ የኢኮኖሚ እድገትን እያሳካች ትገኛለች ብሏል።
እንደ ሲኤንኤን ዘገባ ኢትዮጵያ የወደፊት ዕድገቷን ያፋጥናሉ እንዲሁም ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ኃያልነቷን ያጠናክራሉ ተብለው በሚጠበቁ ኢንዱስትሪዎች ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያደረገች ነው። ዘገባው የዋና ከተማዋን የአዲስ አበባን ትራንስፎርሜሽን ያጎላ ሲሆን፣ በፍጥነት እያደገች ያለችው አዲስ አበባ የሀገሪቱን ሰፊ የኢኮኖሚ ራዕይ እና የዘመናዊነት ጥረቶች ማሳያ መሆኗን ገልጿል።
በተጨማሪም ሲኤንኤን ኢትዮጵያ ወደ 140 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕዝቦች መኖሪያ መሆኗን የጠቆመ ሲሆን፣ ይህም ከአፍሪካ ትላልቅ እና በፍጥነት እያደጉ ካሉ ሀገራት አንዷ ያደርጋታል ብሏል።

ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ልዩ ቃለ ምልልስ የኢንተርናሽናል ግሮዝ ሴንተር (International Growth Center) የሀገር ውስጥ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ መኮንን የኢትዮጵያን ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር (ዴሞግራፊያዊ) ብልጫ አጉልተው አሳይተዋል።
“ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር ሁለተኛዋ ትልቅ ሀገር ናት። ከጠቅላላው ሕዝብ አቅራቢያ 48 በመቶ የሚሆነው ዕድሜው ከ15 ዓመት በታች ሲሆን፣ ወደ 70 በመቶ የሚጠጋው ደግሞ ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች ነው” ብለዋል።
አቶ ቴዎድሮስ አክለውም ሀገሪቱ ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ያስመዘገበችውን አስደናቂ የኢኮኖሚ ዕድገት አጉልተው አሳይተዋል።
“ከ15 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) እና በአንድ ሰው ገቢ (GDP per capita) ስንለካ ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት አማካይ በእጅጉ ያነሰ ነበር። ዛሬ ግን ከአፍሪካ አምስት ወይም ስድስት ትላልቅ ኢኮኖሚዎች አንዷ ለመሆን በቅታለች። ሂደቱ እጅግ አስደናቂ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።
ሲኤንኤን ለኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋፅዖ ያደረገው ከአፍሪካ ትልቁ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (GERD) መጠናቀቅ መሆኑን ገልጿል። ዘገባው ግድቡን በአህጉሪቱ ከተመዘገቡት እጅግ ጉልህ የኢንጂነሪንግ ስኬቶች አንዱ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፣ በዓባይ ወንዝ ዳርቻ የሚገኘውን ሩቅ ሸለቆ የለወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ መሐንዲሶችና የግንባታ ሠራተኞች ከ14 ዓመታት በላይ በፈጀ ሥራ የገነቡት መሆኑን አብራርቷል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ለጣቢያው በሰጡት አስተያየት “ከአቅም አንጻር የግድቡ የኃይል ማመንጫ 5,150 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፣ ለሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከ50 በመቶ በላይ አስተዋፅዖ ያደርጋል” ብለዋል። ሲኤንኤን እንደዘገበው የህዳሴ ግድብ ግንባታ በ2011 (እ.ኤ.አ.) የተጀመረ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ በይፋ ተጠናቆ ተመርቋል።
በግንባታው ወቅት ያጋጠሙትን ፈተናዎች አስመልከተው ኢንጂነር ክፍሌ እንደተናገሩት ከባድ መሣሪያዎችን ወደ ሩቁ የፕሮጀክት ቦታ ማጓጓዝ ከባድ ከነበሩት ተግባራት አንዱ እንደነበር ጠቁመዋል።
“የፕሮጀክቱ ቦታ ከጅቡቲ ወደብ ወደ 1,400 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃል። ከመጠን በላይ ከባድ እና ትላልቅ ጭነቶችን ማጓጓዝ ወደ ግንባታው ቦታ እስኪደርስ ድረስ አንዳንድ ጊዜ ከ60 እስከ 90 ቀናት ይወስድ ነበር” ሲሉ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ሲኤንኤን ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የወጣበት ይህ ፕሮጀክት በህዝብ አስተዋፅኦ፣ በመንግሥት ቦንድ እና በመንግሥት በጀት አማካኝነት ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የተሸፈነ መሆኑን አጉልቶ አሳይቷል።
“የህዳሴ ግድብ በራስ አቅም የተገነባ ፕሮጀክት ነው። ከኢትዮጵያ ውጭ አንዲት ሳንቲም እንኳ አላገኘንም። ከ4.2 እስከ 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመተው አጠቃላይ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት አስተዋፅኦ ብቻ የተሸፈነ ነው” ሲሉ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ለሲኤንኤን ተናግረዋል።